ቀጥታ፡

ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የተደራሽነት ግብ መሳካት ሰው ተኮር ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን የተደራሽነት ግብ ለማሳካት ዘመኑን የዋጁ ሰው ተኮር ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠርና የማምረት ሥራን ቀዳሚ ትኩረቱ አድርጎ እንደሚሠራ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበረውን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ከቀናት በፊት ይፋ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሁሉም ዜጋ በእጅ ስልኩ ካለበት ቦታ የሚፈልገውን አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት ዕድል እንደሚፈጥር ማንሳታቸው ይታወቃል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጄ እንግዳ ( ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ስትራቴጂው የዜጎችን የቴክኖሎጂ እኩል ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አቅጣጫ ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የቴሌኮምና ሌሎች የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽነት እንደሚያሰፋም ነው ያነሱት።

ይህም በዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ ማንም ወደኋላ እንዳይቀር ያስችላል ብለዋል።።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ መሠረት ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን  መፍጠር ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም ነው ዶክተር ደረጄ ያነሱት።

ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰው ተኮር የሆኑና ደህንነታቸው የተጠበቁ ቴክኖሎጂዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተው፥ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሚናውን ይወጣል ብለዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለዩኒቨርሲቲው በሰው ሰራሽ አስተውሎትና ሌሎች የዲጂታል ማዕቀፎች የልህቀት ማዕከልነቱን ለማጎልበት ትልቅ አቅም ፈጥሮለታል።

ለስትራቴጂው ስኬት የሳይበር ደህንነትን የሚያረጋግጡ ቴክኖሎጂዎችን በጥናትና ምርምር በመለየት እንዲሁም ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር ረገድ በርካታ ተግባራትን እናከናውናለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም