ቀጥታ፡

ልማት ላይ በመሳተፍ የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል - የቀድሞ ታጣቂዎች

መተማ፤ ታህሳስ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በሰላም ግንባታና ልማት ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ  የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ተዘጋጅተናል ሲሉ  በምዕራብ ጎንደር ዞን  የሰላም አማራጭን ተቀብለው የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎች ገለጹ።

በዞኑ መተማ ወረዳ ጉባይና ሌንጫ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ታጣቂዎቹ የሰላምን አማራጭ ተቀብለው ሲመለሱ ሙሉ ትጥቃቸውን ለመንግስት በማስረከብ ነው። 

ከተመላሾቹ  መካከል  ብርሃኑ አወቀ  እና ስመኘው አዳነ፤ የተሳሳተ መንገድ ተከትለን  በሕዝብ ላይ በፈጸምነው ጥፋት  ተፀፅተናል ብለዋል።

ግጭት በመፍጠር በአካባቢው ሕብረተሰብ በእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና  ማሳደራችን ተገቢነት እንደሌላው ተገንዝበን ተመልሰናል ሲሉ ገልጸዋል። 

መንግስት ያመቻቸውን የሰላም እድል መምረጣቸውን ገልጸው፤ በጥፋታቸው በመፀፀት በቀጣይ በሰላም ግንባታና ልማት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ  የበደሉትን  ሕዝብ ለመካስ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህንንም  ከመንግስትና ከሕብረተሰቡ ጎን በመሰለፍ  በተግባር ለማረጋገጥ እንጥራለን ብለዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰ አዱኛ በበኩላቸው፤ ሰላምን ማፅናት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶች በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከወይይቱ በኋላ  የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሕብረተሰቡ  ድጋፉን ይበልጥ አጠናክሮ  ሰላምን ለማፅናት በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን  ገልጸዋል።

ወደ ሰላም የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎችም የበደሉትን ሕዝብ ለመካስ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤  የቀሩትም እንዲመለሱ አሁንም የሰላም በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም