ቀጥታ፡

በዞኑ ባለፉት አምስት ወራት ከ45 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች በተለያዩ መስኮች የስራ ዕድል ተፈጥሯል

መቱ፤ ታህሳስ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የኢሉ አባቦር ዞን  ባለፉት  አምስት ወራት  ከ45 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች በተለያዩ መስኮች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የኢሉ አባቦር ዞን የስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተሾመ ገብረወልድ፤ በዞኑ ስራ ፈላጊዎችን በመለየት በማህበራት በማደራጀትና በግል ወደ ስራ ለማስገባት በአገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና ዘርፎችና በቅጥር የስራ ዕድል መፍጠር ላይ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በዚህም በዓመቱ ከ86 ሺህ በላይ  ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ከታቀደው እስካሁን ከ45 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ መሀናቸውን ጠቁመዋል።

በዞኑ ለዜጎች  የስራ እድል ለማሳካት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት አየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ወደ ስራ ለሚገቡ አንቀሳቃሾችም የመስሪያ እና መሸጫ ቦታን ከማመቻቸት ባለፈ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማመቻቸት እንደተቻለም ተናግረዋል።

በዞኑ በተፈጠረላቸው የስራ እድል በትጋት በመስራት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን አንቀሳቃሾቹ ተናግረዋል።

በዞኑ ያዮ ወረዳ በግብርና ልማት የስራ እድል ከተፈጠረላቸው  ነዋሪዎች መካከል አማኑኤል ኢታናና ጓደኞቹ የሽርክና ማህበር በእንቁላል ዶሮ እርባታ ስራ ላይ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆናቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ  አማኑኤል ኢታና ይናገራሉ።

በአምስት መቶ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች የጀመሩት ስራ በቀን ከአራት መቶ በላይ እንቁላል ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን  ማሳደግ ችለዋል።

በሀሉ ወረዳ በከብት ማድለብ ዘርፍ ወደስራ የገቡት  ዋቁማ ሲሳይ፤ አሰፋ ገብረሚካኤል እና ጓደኞቻቸው በሽርክና ማህበር   በመደራጀት ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንግስት ያመቻቸላቸው የብድርና መስሪያ ቦታ ለስራው ውጤታማነት እንዳገዛቸው የሚገልጸው የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ዋቁማ ሲሳይ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም