ቀጥታ፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዜጎች የአኗኗር ዘይቤና ኢኮኖሚ ላይ እመርታ አምጥቷል - የዘርፉ ምሁራን

‎ሀዋሳ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በዜጎች የአኗኗር ዘይቤና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እመርታ ማምጣቱን የዘርፉ ምሁራን ገለፁ፡፡

ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማህበረሰብ ትስስርና ለሀገር ዕድገት ቁልፍ ሚና እንዲያበረክት ታልሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጀመረው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ ምዕራፍ በስኬት ተጠናቋል፡፡

የዚሁ ትግበራ ቀጣይ ምዕረፍ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ  የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት አግዟል።

ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር፣ በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን መፍጠር ቁልፍ ጉዳዮች ሆነው ተቀምጠዋል።

በርዕሰ ጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ የዘርፉ ምሁራን የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ  በዜጎች የአኗኗር ዘይቤና ኢኮኖሚ ላይ እመርታዊ ለውጥ እንዳመጣ ተናግረዋል፡፡


 

በዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ ቴዎድሮስ አሰፋ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዜጎች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን ተጠቅመው የገንዘብ ዝውውርና መሰል ተግባራትን በቀላሉ እንዲፈጽሙ ምቹ ዕድል በመፍጠር አኗኗር ማዘመኑን ገልጸዋል።

የመረጃ ልውውጦችና ኦን ላይን ግብይቶች እንዲስፋፉ በማድረግም በተለይ በርካታ ወጣቶች በዘርፉ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ገቢ እንዲያመነጩ ያደረገ ስትራቴጂ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለተማሪዎች ትምህርታዊ መረጃዎችን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲቀላጠፍ እየተጫወተ ያለው ሚናም ከፍተኛ መሆኑንም ነው የገለጹት

የቴክኖሎጂ መስፋፋት በተለይ በተቋማት የሚሰጠውን አገልግሎት ብቃትና ጥራትን መጨመሩንም አክለዋል።

ይህም የገቢ አሰባሰብ አፈፃፀም እንዲያድግ በሌላ መልኩ ደግሞ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣቱን አስረድተዋል።

በቀጣይም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትግበራን ዕውን ለማድረግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ማስፋት ቁልፍ ተግባር መሆን እንዳለበትም አስታውቀዋል።

በተለይ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን በስፋትና በፍትሐዊነት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠይቅ ነው ያመለከቱት።


 

በዩኒቨርሲቲው የኤሌክትሮኒክ ትምህርት ዳይሬክተር ተስፋዬ ባዩ(ዶ/ር) በበኩላቸው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በየዘርፉ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ለዜህም የመንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የክፍያ ሥርአትን በማዘመን ለዜጎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተሰሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተለይ በአብዛኛው ወጣቶች የሚሳተፉባቸው አዳዲስ የሥራ ዘርፎች እንዲስፋፉ የቴክኖሎጂው ዘርፍ የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

ይህም ወጣቶች በሠለጠኑበት ሙያ ሥራን በመፍጠር ዓለም አቀፍ ገበያዎችን መቀላቀል እንዲችሉ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን እያሳደገ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህ መንገድ ወጣቶችን ወደ ኢኖቬሽን መሳብና በስፋት ማሳተፍ ከተቻለ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያደጉ ሀገራትን ከመከተል ይልቅ መፎካከር የሚያስችል ሰፊ ዕድል ይፈጠራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

ጅምር ተግባራትን በማላቅ ከሚፈለገው ግብ ለመድረስ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂካዊ ዕቅዶችን በሚገባ መተግባር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽና ጥራት ያለው ከማድረግ ባለፈ ቴክኖሎጂን ተቀብሎ በመተማመን መጠቀም የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት ይግባል ብልዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም