ቀጥታ፡

በሀገር ውስጥ የተመረቱ የማዕድን ማቀነባበሪያ ማሽኖች በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ - ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ የጌጣጌጥ ማዕድናትን እሴት በመጨመር በማምረት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ የሚያስችሉ በሀገር ውስጥ የተመረቱ የመቁረጫ፣ የማለስለሻና የቅርጽ ማውጫ ማሽኖች በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የጌጣጌጥ ማዕድናት ልማት ፍኖተ ካርታ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑንም ገልጿል፡፡

ለማዕድን ሚኒስቴር ተጠሪ የሆነው የኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፉን በጥናትና ምርምር፣ በቴክኖሎጂና በአቅም ግንባታ የመደገፍ ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን በዚህም ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ እንዲሁም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

የኢንስቲትዩቱ የአርቴዝናል እና ጌጣጌጥ ማዕድን ልማት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌራ ተጫነ(ዶ/ር) እንደገለጹት ሀገሪቱ ልዩ ልዩ የጌጣጌጥ ማዕድናት ቢኖሯትም እስካሁን የሚፈለገውን ያህል ገቢ ማግኘት አልተቻለም።

ለዚህም ማዕድናቱ እሴት ሳይጨመርባችው ለውጭ ገበያ መቅረባቸው፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆን በምክንያትነት አንስተዋል፡፡

በተጫማሪም የማዕድን አምራች ማህበራት የፋይናንስና የመሠረተ ልማት ችግሮች፤ የከበሩ ማዕድናትን ጥራትና ዋጋ መለየት የሚያስችል የጂሞሎጂ(Gemology) ግንዛቤ አናሳ መሆን የኮንትሮባንድ መስፋፋት ሌላው ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በርካታ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ ኢንስቲትዩቱ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት እያከናወነ ያለውን ተግባራት ለአብነት አንስተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን ለማዕድን መቁረጫ፣ ማለስለሻ እና ቅርጽ ማውጫ የሚያገለግሉ ማሽኖች በሀገር ውስጥ እንዲዘጋጁ መደረጉንና በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

ዘርፉን በዘመናዊ ስርዓት መምራት የሚያስችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን፣ በቅርቡም ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ጨምረው አስታውቀዋል።

የማዕድን ማውጫ አደጋን የሚከላከል የደህንነት ምሰሶ ዲዛይን እና የኢትዮጵያ የጌጣጌጥ ማዕድናት ልማት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅተው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

መሪ ሥራ አስፈጻሚ ጌራ ተጫነ(ዶ/ር) ይህ የተቀናጀ ጥረት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግና ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም