ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ የዜጎችን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል -የዘርፉ ባለሙያዎች

አሶሳ፤ ታኅሣስ 15/2018 (ኢዜአ) ዲጂታል ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥን ከማስፋፋት ባለፈ የዜጎችን ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ሲያስጀምሩ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶች ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ዘርፉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የዜጎችን ተወዳዳሪነት ያሳድጋል።


 

ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ዜጎች ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በዩኒቨርሲቲው የሲስተም አድሚኒስትሬተር ባለሙያ ክብረት በላይ ገልጸዋል።

መንግሥት ለዲጂታል ዘርፉ የሰጠው ትኩረት ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን አንስተው፤ የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት የዜጎችን ሥራ ፈጣሪነት እንደሚያበረታታ አስገንዝበዋል።


 

የዲጂታል ዘርፉን ተደራሽነትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ዝርጋታን በይበልጥ ማስፋፋት እንደሚገባ ያመላከቱት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የኔትወርክ ቡድን መሪ አያሌው ነገሮ ናቸው።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ስኬታማ ለማድረግ በተቋማት ደረጃ የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን በማጠናከር ተጠቃሚዎችም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እንዲገነዘቡ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የዲጂታል ኮርሶችን በመከታተል ዜጎች ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግና ከጊዜው ጋር ተራማጅ በመሆን ራሳቸውን ብቁ ማድረግ እንሚጠበቅባቸውም ነው ባለሙያዎቹ ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም