ቀጥታ፡

ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ የመጠቀም ባህልን በማሳደግ የምርት ብክነትን መቀነስ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ የመጠቀም ባህልን በማሳደግ አርሶ አደሩ የሚያጋጥመውን የምርት ብክነት መቀነስ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በ2017/18 የመኸር ወቅት 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ሔክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ ተገብቷል።

በተሰሩ የተቀናጀ የግብርና ልማት ሥራዎች 20 ነጥብ 9 ሚሊየን ሔክታር መሬት በሰብል መሸፈን እንደተቻለ ተናግረዋል።

በግብርና ሜካናይዜሽን ሥርዓት የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወነ የእርሻ መሳሪያና የግብዓት አቅርቦት ሥራም ከ12 ሚሊየን ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም ሰብል መሸፈኑን አስረድተዋል።

በሰብል ከተሸፈነ የመሬት ገጽታ ላይ 653 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ በተያዘው ዕቅድ መሠረት በቆላማና ወይና ደጋ አካባቢ ውጤታማ ምርት የመሰብሰብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በእስካሁኑ ሂደት 14 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ የነበረ ሰብል መሰብሰቡን ጠቁመው፤ ተሰብስቦ ከተወቃ ሰብልም 322 ሚሊየን ኩንታል ምርት ወደ ጎተራ መግባቱን አስታውቀዋል።


 

ኮምባይነርና ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ የመጠቀም ባህል በማሳደግ አርሶ አደሩ የሚያጋጥመውን የምርት ብክነት ለመቀነስም ከአጨዳ እስከ ጎተራ ድረስ ውጤታማ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ የሰበሰበው ሰብል ጉዳት እንዳይደርስበት በፕላስቲክ ማዳበሪያ፣ የብረት ጎተራና ዘመናዊ የምርት ማከማቻ መጋዘን እንዲጠቀም እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በቀጣይም አርሶ አደሩ በቀሪ ሰብል የመሰብሰቢያ የመኸር ወራት የደረሱ ሰብሎችን በአግባቡ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን መቀነስ እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሮችም በሜካናይዜሽን የእርሻ ሥርዓት በሰብል የተሸፈነ ማሳቸውን በዘመናዊ የግብርና ማሽነሪ በመታገዝ ምርታቸውን የመሰብሰብ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

አርሶ አደር እሸቱ ተስፋዬ፤ ከባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ ወደ ዘመናዊ የግብርና ማሸነሪ የመጠቀም የተደረገው ሽግግር በሰብል ምርታማነት ላይ ከፍተኛ መሻሻል እያስመዘገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የእርሻ ትራክተር፣ ኮምባይነር፣ የሰብል አንክብካቤ ኬሚካል የመጠቀም ባህል በሰብል ምርታማነት ላይ እመርታዊ ውጤት እያመጣ መሆኑን አንስተዋል።


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር ተሾመ ስዩም በበኩላቸው፤ በማኅበር በመደራጀት የተከተሉት ዘመናዊ ግብርና አስተራረስ ዘዴ በግብዓት አቅርቦትና ምርት አሰባሰብ ላይ ውጤት እያስገኘላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም