የኮሚሽኑ ሥራዎች ስኬታማ ሆነው እንዲቀጥሉ ድጋፋችንን እናጠናክራለን--የሀገር ሽማግሌዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኮሚሽኑ ሥራዎች ስኬታማ ሆነው እንዲቀጥሉ ድጋፋችንን እናጠናክራለን--የሀገር ሽማግሌዎች
ወልቂጤ ፤ታህሳስ 15/2018 (ኢዜአ)፡-የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራዎች ስኬታማ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያደርጉትን እገዛ እንደሚያጠናክሩ የጉራጌና የቀቤና ሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ቁርሾዎችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ተግባራዊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ኮሚሽኑ ለልዩነትና ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት አሳታፊ በሆነ መልኩ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በኮሚሽኑ እንቅስቃሴ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉራጌና ቀቤና የሀገር ሽማግሌዎች ኮሚሽኑ ለዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት እስከመጨረሻው ስኬታማ ሆነው ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ለእዚህም የኮሚሽኑ ስራዎች የተሳካ እንዲሆኑ በተለያየ መንገድ ሲያደርጉት የነበረውን አስተዋጾ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ አባል አቶ ተሰማ ተክሉ በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያከናወናቸው ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ ያሉ የማያግባቡን ዋና ዋና ችግሮችን ለይቶ በውይይት ለመፍታት ኮሚሽኑ አካታች በሆነ መንገድ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው፣ ምክክሩ ግቡን እንዲመታ እንደ ሀገር ሽማግሌ ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ለዚህም በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ባህላዊ የግጭት መፍቻ መንገዶችን በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም እሴቶች ግንባታ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ወደፍጻሜ ደርሶ ጠንካራ ብሔራዊ መግባባትና ሀገራዊ አንድነት እንዲፈጠር ጠንክረው እንደሚሰሩም ነው የገለጹት።
ሌላው የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ አባል አቶ እድሪስ መሃመድ በበኩላቸው ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችንና የእርቅ ስርዓቶችን ጥቅም ላይ ማዋል ለኮሚሽኑ ሥራ ስኬታማነት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ቂምና ቁርሾዎችን በይቅርታ ማለፍ ለምክክሩ ሥራ ውጤታማነት የራሱ ሚና እንዳለው ጠቁመው፣ እንደሀገር ለዘመናት ላለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ ሥራዎች ግባቸውን እንዲመቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ አንድነቱን እንዲያጎለብት ከሚሰሩት ሥራ በተጨማሪ የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ ሰላምን የሚያጠናክርበት የአብሮነት እሴቶችን ኮሚሽኑ እንዲጠቀምበት ሚናቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት እያደረገ ላለው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ የቀቤና ሀገር ሽማግሌ መኪ ሁሴን እና ሃያቱ ሻሚል ናቸው፡፡
ልዩነቶችን በውይይት በዘላቂነት መፍታት ለሀገራዊ መግባባት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፣ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ በኮሚሽኑ ለተጀመሩ ሥራዎች ስኬታማነት እገዛቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
ማንኛውም ቅሬታና ልዩነትን በሰላማዊ መንገድና በውይይት ብቻ መፍታት ለሀገር እድገት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት የሀገር ሽማግሌዎቹ፣ የኮሚሽኑ ስራዎች እስከመጨረሻው ለውጤት በቅተው የማየት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።