በዞኑ እስካሁን በበጋ መስኖ ከለማው ውስጥ ከ74 ሺህ ሔክታር በላይ በኩታ ገጠም ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ እስካሁን በበጋ መስኖ ከለማው ውስጥ ከ74 ሺህ ሔክታር በላይ በኩታ ገጠም ለምቷል
አዶላ፤ ታኅሣስ 15/2018 (ኢዜአ)፡- በጉጂ ዞን እስካሁን በበጋ መስኖ ስንዴ ከለማው 92 ሺህ 340 ሔክታር 74 ሺህ 312 ሔክታሩ በኩታ ገጠም መልማቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደስታ ገብረየሱስ ገለጹ።
በበጋ መስኖ ስንዴ 117 ሺህ 350 ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም በማልማት ከ4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ኃላፊው ለኢዜአ ተናግረዋል።
ዘንድሮ በመስኖ ለማልማት የታቀደው መሬት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ17 ሺህ 366 ሔክታር ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።
አዳዲስ የግብርና ኢኒሼቲቮች መተግበራቸውን አንስተው ለአብነትም፤ በትራክተር ማረስ፣ የመስመር እና የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን መከተል፣ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አጠቃቀም ማደግ የሚሉትን ጠቅሰዋል።
የመስኖ ልማቱን የሚያግዙ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች ለአርሶ አደሮች መቅረቡንም ጠቁመዋል።
በበጋ መስኖ ልማቱ 213 ሺህ 774 አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑንም አንስተዋል።
በዞኑ አናሶራ ወረዳ የራያ ቦዳ ቀበሌ ነዋሪ በቀለ ዱጎ፤ በበጋ መስኖ ልማት በኩታ ገጠምና የመስመር አስተራረስ ዘዴን በመከተል ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው እያለሙ መሆናቸውን ገልጸው ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።