ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር በቴክኖሎጂ የመጠቀም ዕድልን በማመቻቸት ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር በቴክኖሎጂ የመጠቀም ዕድልን በማመቻቸት ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል
ሮቤ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፡- ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መተግበር በኢትዮጵያውያን ዘንድ በቴክኖሎጂ የመጠቀም ዕድልን በማመቻቸትና በማስፋት ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰሞኑን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት በሰጡት ማብራሪያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በስኬት እንደተጠናቀቀ መግለጻቸው ይታወሳል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት በብዙ መልኩ የሚገለጽ መሆኑንና የተቋማት የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ መጠናከር በተለይም ደግሞ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ለዘርፉ ስኬት ጥሩ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ የዘርፉ ምሁራን፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በቴክኖሎጂ የመጠቀም ዕድልን በማመቻቸትና በማስፋት ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት መምህርና የኮምፕቲንግ ኮሌጅ ዲን ሚሊዮን ስሜ፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዘርፉ እድገት ትልቅ መሰረት ማኖሩን ተናግረዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ በቴሌ ብር፣ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴ መስፋፋት፣ ዲጂታል ፋይዳና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ሕዝቡ መጠቀም እንዲጀምር እድል መፍጠሩን አብራርተዋል።
በተለይም እንደ መሶብ ዓይነት መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል ለመስጠት የተጀመሩ ሥራዎች የዘርፉ ስኬቶች ማሳያና ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ፣ የመንግስት ገቢን መጨመርና የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት ላይ አበረታች ስኬቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የማኔጅመንትና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ሁሳ አሎ ናቸው።
በተለይም በሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት መሸጋገሯ ለስኬቱ በማሳያነት አንስተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ም ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መሠረት በማድረግ በመዘጋጀቱ በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ መደላድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
የዩኒቨርሲቲው የኢንፎርሜሽን ሲስተም መምህርና የኮምፒቲንግ ኮሌጅ የምርምርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዲባባ አደባ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በአገልግሎት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን አስታውሰዋል።
ለአብነትም ከማዕከል እስከ ወረዳ የተዘረጋው የዲጂታል ትስስር ለዚህ ተጠቃሽ ስኬትና የበለጠ ሊስፋፋ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።