ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ሚናው የጎላ ነው - ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ሚናው የጎላ ነው - ቢሮው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት የመንግስትና የህዝብን ውስን ሃብትና በጀት ለታለመለት ዓላማ ከማዋልና ብልሹ አሰራሮችን ከመከላከል ባለፈ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው የላቀ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ገለጸ።
የዲጂታል አሰራር ወቅቱ የሚጠይቀውና ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት እንዲኖር ከማስቻሉ ባለፈ፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።
በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከልና የመንግስትን ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ወሳኝ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ሃላፊዎች ይገልፃሉ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አብዱልቃደር ሬድዋን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማን "ስማርት ሲቲ" የማድረግ ግብ እውን እንዲሆን የተቋማት ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት አሰራራቸውን ዲጂታላይዝ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ይህም ፈጣን አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ ተገልጋዮች ባሉበት ቦታ ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙና ብልሹ አሰራሮችን መከላከል የሚያስችል ነው ብለዋል።
ቢሮው እስከ አሁን የሂሳብ ሪፖርቶችን፣ በጀትን፣ የሰራተኛ ደመወዝና የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን ዲጂታል ማድረጉን ያስታወቁት ኃላፊው፤ በቀጣይም ተጨማሪ አገልግሎቶችን በዲጂታል ለማስጀመር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ስነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የፋይናንስ ዕቅድና በጀት ዳይሬክተር ተባረክ ዮሴፍ በበኩላቸው፤ በተቋም ውስጥ ዲጂታል አሰራር መስፈኑ የተፈቀደው ውስን የመንግስት በጀት ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል በማድረግ ረገድ ትልቅ ፋይዳ አለው።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አቃቂ ቃሊቲ ቅርንጫፍ የሂሳብ ባለሙያ ወይዘሮ ሽታዬ ገብረ፤ ዲጂታል የፋይናንስ አሰራር ስራን ለማቀላጠፍ፣ የስራ ግድፈትን ለማረምና ጊዜን ለመቆጠብ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታህሳስ 11 ቀን 2018 ዓም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ይፋ ባደረጉበት ወቅት በሕዝብ መገልገያ ዲጂታል መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን መግለጻቸው ይታወቃል።
ኢትዮጵያ ወሳኝ በሚባል ደረጃ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት ወደ ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት መሸጋገሯን መግለጻቸውም እንዲሁ።