የሚዛን አማን ከተማ ልማት የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነትና ዘመናዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሚዛን አማን ከተማ ልማት የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነትና ዘመናዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተከናወነ ነው
ሚዛን አማን፣ ታኅሣሥ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የሚዛን አማን ከተማ ልማት የነዋሪዎቿን ተጠቃሚነትና ዘመናዊነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ብዝኃ ከተሞች አንዷ ሚዛን አማን ከተማ ለቱሪዝም እና ኢንቨስትመንት ምቹና ተመራጭ ከተማ እየሆነች ትገኛለች።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ኢንጂነር ሰሎሞን ሌዊ፤ በመደመር መንግስት እይታ የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ውብ ጽዱና ለኑሮ ምቹ የማድረግ ስራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት የሚዛን አማን ከተማን ግንባታ ዘመኑን የዋጀ የኢንቨስተሮችንና የጎብኝዎችን ቀልብ የምትገዛ እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በገጠርም ይሆን በከተማ ትውልድን ታሳቢ ያደረገ የዲጅታል ልማትን ማፋጠን፣ ጤናማ የመኖሪያ አካባቢዎችን የመፍጠርና መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።
በከተማዋ ከኮሪደር ልማት ባሻገር በተመረጡ ማዕከላት የ"ስማርት ሲቲ" ግንባታ ለመጀመር የጥናት እና ፕላን ዝግጅት ሥራ እየተካሔደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ሰው ተኮር በመሆን የአኗኗር ዘይቤን ቀለል የሚያደርጉ፣ ዘመንን የዋጁ እና ትውልድን መሰረት ያደረጉ መሆኑን አንስተው ሚዛን አማን በዚሁ ልክ እየተሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፍሬሕይወት ከበደ እና አቶ ቤላ ኮይ፤ የሚዛን አማን ከተማ ውበትና ለውጥ የሚታይ መሆኑን ገልጸው ስራዎቹ ከተማዋን ወደ ትልቅ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው ብለዋል።
በከተማዋ በተለየ ፍጥነትና ጥራት ግንባታዎች እየተከናወኑ እየተጠናቀቁም ለአገልግሎት እየበቁ መሆኑን ተናግረው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።