ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል 

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ባህር ዳር ከተማ ከፋሲል ከነማ ይጫወታሉ።

ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በሶስቱ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። ቡድኑ በ13 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በሊጉ እስከ አሁን 10 ጨዋታዎች በአምስቱ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አምስት ጊዜ አቻ ወጥቷል። በ20 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። 

ፋሲል ከነማ  በሊጉ እስከ አሁን በሊጉ ሽንፈት ያላስተናገደ ብቸኛው ቡድን ነው። የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ከሲዳማ ቡና ይረከባል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር አርባምንጭ ከተማ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ምንም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። በአምስቱ ሲሸነፍ አምስት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ በ20 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው መቀሌ 70 እንደርታ በሊጉ እስከ አሁን ሶስት ነጥብ አላገኘም። በአምስቱ ጨዋታዎች ሲሸነፍ አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። ቡድኑ በተመሳሳይ አምስት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 19ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይፋለማሉ። 

ነጌሌ አርሲ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አዲስ አዳጊው ነጌሌ አርሲ በ13 ነጥብ ደረጃን ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በስምንት ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ሀድያ ሆሳዕና በ10 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ወላይታ ድቻ በተመሳሳይ 10 ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት እስከ ታህሳስ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ሲዳማ ቡና ሊጉን በ21 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም