የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገር ሱዳን ከአልጄሪያ ጋር ትጫወታለች - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገር ሱዳን ከአልጄሪያ ጋር ትጫወታለች
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
በዕለቱ የምድብ አምስት እና ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በምድብ አምስት የምስራቅ አፍሪካዋ ሱዳን ከአልጀሪያ ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ትጫወታለች።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የአፍሪካ ዋንጫ መስራች ሀገር ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው ሱዳን በውድድሩ ላይ ስትሳተፍ የአሁኑ ለ10ኛ ጊዜ ነው። እ.አ.አ በ1970 ራሷ ያዘጋጀችውን ሰባተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ጋናን በማሸነፍ አንስታለች።
ሱዳን እ.አ.አ በ1957 ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ያዘጋጀች ታሪካዊ ሀገር ናት።
ተጋጣሚዋ አልጄሪያ በአፍሪካ ዋንጫው ለ19ኛ ጊዜ ተሳትፎዋን ታደርጋለች። የሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር የ17ኛው እና የ32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች አሸናፊ ናት።
በዚሁ ምድብ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ቡርኪናፋሶ ከኢኮቶሪያል ጊኒ በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካው ዋንጫ ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል። ኢኮቶሪያል ጊኒ እ.አ.አ በ2015 ባዘጋጀችው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ አንድ ተገናኝተው ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ቡርኪናፋሶ በአፍሪካ ዋንጫው ለ14ኛ ጊዜ እንዲሁም ኢኳቶሪያል ጊኒ ለአምስተኛ ጊዜ ተሳትፏቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። ሁለቱም ሀገራት የአፍሪካ ዋንጫን አንስተው አያውቁም።
በተያያዘም የምድብ ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ ኮትዲቭዋር ከሞዛምቢክ በማራካሽ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሀገራቱ በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
እ.አ.አ በ1986 በግብጽ በተካሄደው 15ኛው የአፍሪካ በምድብ ተገናኝተው ኮትዲቭዋር 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ1996 ባዘጋጀችው 20ኛው የአፍሪካ ዋንጫም በምድብ አራት ተጫውተው ኮትዲቭዋር 1 ለ 0 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
በአፍሪካ ዋንጫው ለ25ኛ ጊዜ የምትሳተፈው ኮትዲቭዋር ሶስት ጊዜ ዋንጫ አንስታለች። በአንጻሩ ለስድስተኛ ጊዜ የምትሳተፈው ሞዛምቢክ ከዚህ ቀደም በነበራት ተሳትፎ ከምድቧ አልፋ አታውቅም።
በዚሁ ምድብ ካሜሮን ከጋቦን ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በአጋዲር ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ዋንጫ ለአምስት ጊዜ ተገናኝተው ጋቦን አንድ ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ካሜሮን በአፍሪካ ዋንጫው ለ22ኛ ጊዜ የምትሳተፍ ሲሆን አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ስኬታማ ሀገር ናት።
በውድድሩ ላይ ዘጠነኛ ተሳትፎዋን የምታደርገው ጋቦን በበኩሏ ትልቁ ውጤቷ በ20ኛው እና 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ የደረሰችባቸው ናቸው።
ካሜሮን በአፍሪካ ዋንጫው ለመጀመሪያ ጊዜ ጋቦንን ለማሸነፍ ትጫወታለች።