ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሀገርን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ያሸጋግራል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሀገርን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ያሸጋግራል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሀገርን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ በማሸጋገር የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መሰረት በማድረግ መዘጋጀቱን በወቅቱ አንስተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሦስት ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህም ተደራሽነትን ማስፋት፤ እኩል እድል ማመቻቸትና በተቋማትና ህዝብ መካከል መተማመንን መፍጠር መሆናቸውን አብራርተዋል።
የኢንፎርሜሽንና መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሳይበር ደህንነት ላይ በርካታ አስቻይ መሰረቶች መጣላቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የራሳችንን የክላውድ መሰረተ ልማት በመገንባት በኢትዮጵያ የዲጂታል አገልግሎት መተማመን መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ለጸጥታ ተቋማትም የዲጂታል ፎረንሲክ ቤተ ምርመራ በመገንባት ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ጠቁመው፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የሳይበር ደህንነት ስትራቴጂካዊ ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
በዚህም የማይበገር ቁልፍ የዲጂታል መሰረተ ልማት መገንባት፣ የህዝብ መሰረተ ልማትን ማዘመን፣ የአደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከል የማቋቋምና የግል ተቋማትን ያካተተ የሳይበር ደህንነት ስራ እንዲጎለብት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር)፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስነ-ምህዳር ማስፋት የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የራሳችንን ክላውድ ከመጠቀም ባሻገር ውጤታማ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡
በዚህም በተደራጀ አግባብ መረጃዎች ለውሳኔ አሰጣጥ እንዲውሉ የሚሰራ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ ገለልተኛ ብሔራዊ የመረጃ ባለስልጣን ወደ ስራ እንዲገባ ይደረጋልም ነው ያሉት።
ዲጂታል አገልግሎቶችን የማናበብና ወጥ የማድረግ ስራ ላይም ትኩረት መሰጠቱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በቴሌኮም ዘርፍ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን አስታውቀዋል።
ለአብነትም የሞባይል ደንበኞች ቁጥርን 97 ሚሊየን ማድረስ የተቻለ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 57 ሚሊየኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አንድ ሺህ ሰለሳ ከተሞች የ4ጂ ኔትወርክ ተደራሽ መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር 128 ሚሊየን ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል።
የ5ጂ ኔትወርክ ሽፋንም ለ100 ከተሞች ይደርሳል ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፡፡
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የዲጂታል ክፍያን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አኳያ አሁን ካለበት ከሰባት እጥፍ በላይ እንዲያድግም በልዩ ትኩረት ይሰራልም ብለዋል፡፡
በዲጂታል ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ስራዎች የመደመር መንግስት በቀለለ ቢሮክራሲ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መግለጻቸውም ይታወሳል።