ቀጥታ፡

ወጣቶች የመደመር መንግስት እሳቤን እውን በማድረግ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ ወጣቶች የመደመር መንግስት እሳቤን እውን በማድረግ የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የሲዳማ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽንና ወጣቶቸ ማህበር “የተደመረ የወጣት አደረጃጀት ለሀገር ልማት እመርታ” በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር ጉባኤ በሀዋሳ አካሂዷል።

በጉባኤው የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ እመቤት ኢሳያስ እንዳሉት፤ ወጣቱ በክልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ወጣቶች ሚናቸውን ሊያጠናክሩ  ይገባል።

ለዚህም በመደመር መንግስት እሳቤ የወጣቶችን አቅም በመገንባት  ልማቱን ለማፋጠን  ትኩረት መሰጠቱን አንስተዋል።

የወጣቱን የስራ እድል ፈጠራ ለማሳደግም የክህሎት ስልጠናና የመስሪያና የመሸጫ እንዲሁም የብድር አገልግሎት አንዲያገኙ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የቢሮው ምክትልና የወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ደስታ ለገሰ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በከተማና በገጠር በሚከናወኑ የልማት ስራዎች የወጣቱ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱንም  ጠቁመዋል።

የወጣቶች ፌዴሬሽንና ማህበር የጋራ ጉባኤው በመደመር እሳቤ ጠንካራ አደረጃጀት እንዲኖር ለማድረግና አመራሩን በአዲስ መልክ እንዲሰይም ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በጉባኤው የክልሉ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ የተመረጠው ወጣት ምንተስኖት መኩሪያ በበኩሉ ለሀገር ልማትና  ሰላም  ወጣቱ የነቃ የዜግነት ተሳትፎውን  እንዲያሳድግ  እንሰራለን ብሏል።


 

በዚህም እንደ ወጣት ጠቃሚ ስራ በመስራት ለክልሉም ሆነ ለሀገር ብልጽግና ጉዞ መሳካት የድርሻውን ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።

የፌዴሬሽኑ አባል የሆነችው ወጣት ዘላለም ሰለሞን በበኩሏ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲጎለብት ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውሳለች።

ተግባሩንም በማስቀጠል ወጣቶች በሀገር ጉዳይ በንቃት እንዲሳተፉ በማስተባበር የበኩሏን እንደምትወጣም ገልጻለች።

በጉባኤው የተለያዩ ክልሎች ፌዴሬሽን አመራሮች፣ ከሲዳማ ክልል አራት ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የወጣት ማህበራትና ፌዴሬሽን አደረጃጀቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም