ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና አሜሪካ የጤና ትብብር ስምምነት ጠንካራ አጋርነታቸውን የሚያሳይ ነው - ሚኒስትር አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና አሜሪካ ዛሬ የተፈራረሙት የጤና ዘርፍ የትብብር ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር  አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ኢትዮጵያና አሜሪካ በጤናው ዘርፍ በአጋርነት መስራት የሚያስችላቸውን የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የጋራ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

የትብብር ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ፈርመውታል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ምዕተ-ዓመት የተሻገረና በጠንካራ ወዳጅነት ላይ በተመሰረተ ስትራቴጂክ አጋርነት የተገነባ ነው ብለዋል።

ሀገራቱ በበርካታ መስኮች ጠንካራ አጋርነት እንዳላቸው በማንሳት፥ በተለይ በጤናው ዘርፍ የዜጎችን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሟላት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚተገበረው የትብብር ስምምነትም የሀገራቱን ጠንካራ አጋርነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የጤና ኢንቨስትመንት ስርዓትን የሚያጠናክር አዲስ የጤና አጋርነት ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የፋይናንስ አጋርነትና ድጋፉን ለታለመለት የጤና ሥርዓት ማሻሻያ ለማዋል በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ÷ ስምምነቱ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካን የጤና ዘርፍ ትብብርን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።

የትብብር ስምምነቱም እ.አ.አ ከ2026 እስከ 2030 ድረስ ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይ በማንሳት፥ የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታዎች መከላከል ሥራዎችን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።

የትብብር ማዕቀፉ በኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ ቲቢ፣ ወባ፣ የእናቶች እና ህጻናት ጤናን ጨምሮ የበሽታ መከላከል እንዲሁም የወረርሽኝ ምላሽ እና ዝግጁነትን የሚያጠናክር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮ-አሜሪካ የአጋርነት ትብብር የማይበገር የጤና አገልግሎት ሥርዓት ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ÷ ኢትዮጵያና አሜሪካ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የገነቡ ሀገራት ናቸው ብለዋል።

በጤናው ዘርፍ የተፈረመው የትብብር ስምምነት ኢትዮጵያ የጤና ሥርዓቷን ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ አሜሪካ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረትም የጤና ሥርዓቱን ጠንካራ ምላሽ ሰጪነት ለማረጋገጥ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም