በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ17ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት ይሸፈናል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ17ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት ይሸፈናል
ዲላ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ያረጀ ቡና በማንሳትና ማሳውን በማስፋት ከ17ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡናና ቅመማቅመም ባለስልጣን ገለጸ።
ቡናን በኩታ ገጠም በማልማት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ አቅም የማሳደጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አማኑኤል ብሩ ተናግረዋል።
ቡናን በኩታ ገጠም የማልማት ኢኒሼቲቭ በክልሉ ጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ዛሬ በባለድርሻ አካላት የመስክ ምልክታ ተካሂዷል።
የክልሉ ቡናና ቅመማቅመም በወቅቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ የቡና ማሳን በማስፋትና በማደስ የዘርፉን ልማት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
ለአብነትም ባለፈው ዓመት ከ7ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና በማልማት የክልሉን የቡና ሽፋን ወደ 235 ሺህ ሄክታር ማሳደጉንና ከዚህም ውስጥ በኩታ ገጠም የለማ እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎች የማቅረብና በኩታ ገጠም ማልማት ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ተግባሩን በማስቀጠልም በተያዘው በጀት ዓመት ያረጀ ቡና በማንሳትና ማሳውን በማስፋት ከ17ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት ለመሸፈን በሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥም ከ3ሺህ 707 ሄክታር በኩታ ገጠም ይለማል ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ለዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት፣ የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎች አቅርቦትና አስፈላጊ ግብዓቶች ማቅረባቸውን አንስተዋል።
በዞኑ ዝርያቸው የተሻሻሉ ቡናን ማልማት ምርታማነትን ከማሳደጉ ባለፈ ምርቱ የሚደርስበትን ጊዜውን ማሳጠር መቻሉን የገለጹት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ሃላፊ ተገኝ ታደሰ ናቸው።
በዞኑ የኩታ ገጠም የቡና ልማት አርሶ አደሩንና ቀበሌዎችን በልማት እያስተሳሰረ ነው ያሉት ሃላፊው፤ ለአብነትም በወናጎ ወረዳ የቱማታ ጭራቻና ጦቅቻ ቀበሌዎች መካከል የሚገኘው አንድ መቶ ሄክታር ኩታ ገጠም ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
በወናጎ ወረዳ ቱማታ ጭራቻ ቀበሌ አርሶ አደር አስራት ጨበሶ በሰጡት አስተያየት፤ በቀበሌያቸው እሳቸውን ጨምሮ አንድ መቶ አርሶ አደሮች ቡናን በኩታ ገጠም እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ የተሻሻለው የቡና ዝሪያ ድርቅና በሽታ ከመቋቋም ባለፈ በሁለት ዓመት ውስጥ የመጀመሪያ ምርት ለመስጠት አበባ መያዙ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።