ቀጥታ፡

የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ለሕግ የበላይነት መከበር የበኩላችንን እንወጣለን-የመተማ ወረዳ ነዋሪዎች

መተማ፤ ታህሳስ14/2018 (ኢዜአ):-የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ለሕግ የበላይነት መከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ አስተዳደር ነዋሪዎች ተናገሩ።

በመተማ ወረዳ ጉባይ ጀጀቢት ከተማ ዘላቂ ሰላም ግንባታን መሰረት ያደረገ ሕዝባዊ ውይይት ዛሬ ተካሄዷል። 


 

በውይይት መድረኩ ላይም ነዋሪዎቹ ፤ የአካቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ለሕግ የበላይነት መከበር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሙሉነህ ጥጋቡ ፤ በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም በማፅናት ልማት እንዲጠናከር የሚደግፉ መሆኑን ገልጸዋል። 

ሕግ የማስከበር ተግባር ተጠናክሮ  የሰፈነውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ  የድርሻቸውን እንደሚወጡም  ተናግረዋል።

ሌላኛው ተሳታፊ አቶ ክፍሌ ለጋስ ፤ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። 

ለሁሉም ነገር ሰላም  አስፈላጊ ነው ያሉት  ቄስ አሰፋ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ መንግስት ለዘላቂ ሰላም እያደረገ ያለውን ተግባር እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።  

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ ጌጡ እንዳሉት፤ሕዝቡ በሰላም ማስከበር ተግባር የነቃ ተሳትፎውን ይበልጥ ማጠናከር  ይኖርበታል። 

መንግስት ሰላምን ለማፅናት እያደረገ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር ውጤት እያመጣ መሆኑን አንስተዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰ አዱኛ፤ መንግስት ከሕግ ማስከበር ስራ ጎን ለጎን  የሰላም አማራጭን ለሚቀበሉ  በሆደ ሰፊነት አሁንም በሩን ከፍቷል ብለዋል። 

ሆኖም በሽፍትነት  በመቀጠል ሕዝቡን ሰላም በሚነሱት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም