ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘላቂ ጥቅም ያስገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘላቂ ጥቅም ያስገኛል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 15/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የንግድ ልውውጥ እና የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዘላቂ ጥቅም እንደሚያስገኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል አማካሪ ሚሪያም አሊ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ይፋ ማድረጋቸው ይታወቃል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዲጂታል አማካሪ ሚሪያም አሊ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 የዘመናችን በራሷ የምትተማመን ኢትዮጵያ፣ ብልጽግና በሁሉም ክልሎቿ ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁልፍ ስትራቴጂ መሆኑን አመልክተዋል።
ስትራቴጂው ለእያንዳንዱ ዜጋ የሚያገለግል፣ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያዘምን፣ ኢኮኖሚን የሚያሳድግና እያንዳንዱ ዜጋ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት እንዴት ተሳትፎ ማድረግ እንደሚችል እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ያስፈለገው የሰው ሰራሽ አስተውሎት በፍጥነት ማደግ፣ የዜጎች ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት የማግኘት መሻት እና የንግድ ዘርፉ የበለጠ በዲጂታል ዘርፍ መደገፍ ወሳኝ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጀመረችው የዲጂታል ጉዞ በቁርጠኝነት ካልቀጠለች የዲጂታል ክፍፍል እየሰፋ ይመጣል ያሉት አማካሪዋ ስትራቴጂው ያንን ክፍፍል የሚያጠብ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አካታች ሉዓላዊ እና በግልጽ አላማ የሚመራ መሆኑንም ነው ጨምረው ያብራሩት።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መሰረት ጣይ እንደሆነ ገልጸው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የበለጠ ዘርፉን በጥልቀት እንደሚያሰፋ ገልጸዋል።
ይህም ከሙከራ ፕሮጀክቶች ወደ ሀገር አቀፍ ስርዓቶችና ከተከፋፈሉ አሰራሮች ወደ ተቀናጁ አገልግሎቶች ለመሸጋገር ያስችላል ነው ያሉት።
ሰዎች እና ተቋማትን ማብቃት፣ ሁሉን አቀፍ ዲጂታል ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ አካታች የኢኮኖሚ እድገት ማፋጠንና ኢትዮጵያ ዋነኛ የዲጂታል መዳረሻ ማድረግ የስትራቴጂው የስኬት መለኪያዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ትስስር እና ተአማኒነት የስትራቴጂው ምሰሶዎች መሆናቸውንም ነው ጨምረው አማካሪዋ የገለጹት።
በስትራቴጂው አማካኝነት የህዝብ ዲጂታል መሰረተ ልማት የመንግስት አገልግሎቶችን በማዘመንና የዲጂታል አሰራሮችን በማስፋት ዘላቂ የኢኮኖሚ ጠቀሜታን የማስገኘት ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
ከቴክኖሎጂ በተጨማሪ ስትራቴጂው ህጎች፣ መረጃዎች፣ ክህሎት እና ታማኝነት ወሳኝ መሆናቸው በግልጽ መቀመጡን አስረድተዋል።
ስትራቴጂው ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት እና ኢንዱስትሪን እንዲሁም ሌሎች ዘርፎችን ያካተተ፣ ሀገር በቀል እና ሰውን ያማከለ እንደሆነም ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሃይል እና የኢንተርኔት ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የተሻሻለ የህዝብ አገልግሎት መዘርጋት፣ ዳታ ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን መስጠት፣ የግል ዘርፍ አቅምን ጠንካራ ማድረግ፣ ለሳይበር ጥቃት በቂ የመከላከል ዝግጁነት መገንባትና ኢትዮጵያን የዲጂታል መሪነት ማጎናጸፍ የስትራቴጂው መዳረሻ ግቦች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የዲጂታል አማካሪዋ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።