ቀጥታ፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ትኩረት ተሰጥቶታል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ የማድረግ ስራ ይከናወናል ሲሉ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሄ አርአያሥላሴ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ባቀረቡት ማብራሪያ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ፣ የመንግስት ገቢን መጨመርና የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ ዮዳሄ አርአያሥላሴ፤ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ቁልፍ ጉዳይ ሆኖ መተግበሩን አስታውቀዋል።

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን ማዳረስ በመንግስት የመቶ በመቶ እቅዶች ውስጥ መካተቱን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት 30 ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ፋይዳ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ የማድረግ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሀገራዊ ንቅናቄ በማድረግ 90 ሚሊየን ዜጎችን የፋይዳ መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ በበኩላቸው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂዎች በዜግነት አገልግሎት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ተናግረዋል።

ለአብነትም በአዲስ አበባ ከማዕከል እስከ ወረዳ የተዘረጋው የዲጂታል ትስስር ለዚህ ተጠቃሽ ስኬት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

በሀገር ውስጥ አቅም የለሙ መተግበሪያዎች ለቤተሰብ ምዝገባ፣ ለወሳኝ ኩነትና ለነዋሪዎች አገልግሎት መዋል መጀመራቸውን ገልጸው፤ ይህም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተቋማትን በመረጃ ለማስተሳሰር መሰረት ተጥሏል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም