ቀጥታ፡

የመዲናዋ የኮሪደር ልማት የአካል ጉዳተኞችን ደህንነትና ተጠቃሚነት በማስጠበቅ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ የተከናወኑ የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ስራዎች የአካል ጉዳተኞችን ደህንነትና ተጠቃሚነት በማስጠበቅ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ይህንን የገለጸው "አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማህበራዊ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ ሲከበር የቆየውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በከተማ ደረጃ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ባከበረበት ወቅት ነው።


 

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ እንደተናገሩት፣ በመዲናዋ የተሰሩ የኮሪደር ልማቶች አካል ጉዳተኞች በመንገዶችና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

መንገዶች ራሳቸውን የቻሉ ምቹ የአካል ጉዳተኛ መስመር እንዲኖራቸው፣ ተቋማትም የአካል ጉዳተኞች መተላለፊያ መሰረተ ልማቶችን እንዲያሟሉ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።

አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ያደረጉ ሌሎች የልማት ሥራዎችም መከናወናቸውን በመጥቀስ፥ በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አካታች የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በቢሮው የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋውያንና የቤተሰብ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት በቀለ በበኩላቸው፣ አካል ጉዳተኞችን በሙያ ስልጠናና በግብዓት በመደገፍ ሰርተው ህይወታቸውን እንዲለውጡ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ይታጠቁ ደረሰ፣ በመዲናዋ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ለአብነትም መንገድን ጨምሮ ምቹ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን በማንሳት፥ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በማጠቃለያ መድረኩ የእጅ ሥራ ምርቶቻቸውን ያቀረቡ አካል ጉዳተኛ አምራቾች በሰጡት አስተያየት የኮሪደር ልማቱ ለአካል ጉዳተኞች እንቅስቃሴና የሥራ ውጤታማነት ምቹ ምህዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።

ባገኙት የሙያና የግብዓት ድጋፍ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፥ ይበልጥ ለማሳደግ የመስሪያ ቦታ፣ የገበያ ትስስርና ተከታታይነት ያለው የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም