መገናኛ ብዙሃን በብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ላይ ስራዎቻቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን በብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅና አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ላይ ስራዎቻቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፡- መገናኛ ብዙሃን ብሄራዊ ጥቅምን በማስጠበቅና አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት ረገድ የጀመሯቸውን ስራዎች ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ የኢዜአ እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድሬዳዋ ቅርንጫፎች፣ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም ቅርንጫፍ እና የምርጫ ቦርድን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው አባልና የዘርፉ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዛራ ቢፍቱ፤ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መረጃዎችን ለሕዘብ ተደራሽ በማድረግ የላቀ ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
የሚዲያ ተቋማቱ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን ከመዘገብ ባለፈ ለብሔራዊ መግባባት፣ ለጋራ ትርክት ግንባታና ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የጀመሯቸውን ስራዎች ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በድሬዳዋ የሚገኙትን የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም ቅርንጫፍና የምርጫ ቦርድ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የዴሞክራሲ ተቋማቱ በጠንካራ አደረጃጀት አቅማቸውን በማጎልበት በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
ከጉብኝቱ በኋላም ከድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አብዲ ሙክታር እና ከምክር ቤቱ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።