ቀጥታ፡

በሳይበር ደህንነት ወር የህብረተሰቡን ንቃተ-ህሊና ማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ በስድስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የዜጎችንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማጎልበት የሚያስችል ስራ መከናወኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ገለጹ።

"የሳይበር ደህንነት የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥቅምት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር የማጠቃለያ እና የእውቅና መርኃ ግብር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ ለሳይበር ደህንንት ወሩ ስኬታማነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የዘንድሮው የሳይበር ደህንነት ወር በስሉጥ ከተማ ግንባታ እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መከላከል ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቁመዋል።

በዚህም አቅምን ከመገንባት አኳያ ትልቅ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው የህበረተሰቡንና የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማጎልበት የሚያስችል ስራ መከናወኑን አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ዜጎች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልጸው አስተዳደሩ ለባለተሰጥኦ ወጣቶችና ታዳጊዎች ስልጠና በመስጠት እያበቃ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

ወሩ ሀገር በቀል እውቀቶችን በስፋት ማስተዋወቅ የተቻለበት መሆኑን አንስተው ወጣቶች ያሏቸውን የሳይበር ደህንነት ክህሎቶች በተለያዩ ውድድሮች ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

በወሩ በአጭር ፊልም ውድድር አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡት ዘር አዳም አሰፋ እና አቤነዘር አዲስ በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እና በስልክ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ዙሪያ የሠሯቸው ፊልሞች ለሽልማት እንዳበቋቸው ተናግረዋል።

የተሰጣቸው እውቅና ለላቀ ስኬት የሚያነሳሳ መሆኑን በመጥቀስ፥ በቀጣይ በመሰል ሀገራዊ ሥራዎች ላይ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም