በባንኩ ለአርሶ አደሩ የተመቻቸው የብድር አማራጭ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በባንኩ ለአርሶ አደሩ የተመቻቸው የብድር አማራጭ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
ሆሳዕና፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአርሶ አደሩ ያመቻቸው የብድር አማራጭ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዝ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ባንኩ በግብርናው ዘርፍ አርሶ እና አርብቶ አደሩን ለመደገፍ ባመቻቸው የብድር አማራጭ ላይ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ከባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ መክረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተመቻቸው የብድር አማራጭ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት የሚያግዝ ነው፡፡
በክልሉ ግብርናን በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ቢሆንም የማሽነሪ አቅርቦት ውስንነት እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ ለተለያዩ የግብርና ማሽነሪዎች መግዣን ጨምሮ ለአርሶ አደሮች ያመቻቸው የብድር አቅርቦት በዘርፉ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር ያግዛል ነው ያሉት።
በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጨማሪ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የወጣቶችን ከዘርፉ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሶላር ሀይል አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።
በባንኩ ለግብርናው ዘርፍ የተመቻቸውን የብድር አቅርቦት በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር እንደሚገባም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሪቴይል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ደሳለኝ አለሙ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ባንኩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ያካተተ የብድር አቅርቦትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።
አርሶ አደሩም በተሰማራበት የግብርና ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን የአነስተኛና የረዥም ጊዜ የብድር አቅርቦት መመቻቸቱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በዘርፉ የሚመነጨውን ኢኮኖሚ ከማሳደግ በተጨማሪ ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለገበያ ማረጋጋትና መሰል ያሉትን ጠቀሜታዎች ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ባንኩ ከአርሶ አደሩ የብድር ፍላጎት ጋር ተያይዞ የሚነሱ የዋስትና ጥያቄ ችግሮችን ለመፍታት ካርታን በዋስትና ማቅረብ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አህመድ ሀቢብ እና የክልሉ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ተመስገን ጎዴቦ ተገኝተዋል።