የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት ለዘርፉ ቀጣይ ልማት እና እድገት ጠንካራ መሰረት ጥሏል - የዘርፉ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት ለዘርፉ ቀጣይ ልማት እና እድገት ጠንካራ መሰረት ጥሏል - የዘርፉ ምሁራን
አዳማ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት በቀጣይም ለዘርፉ ልማት እና እድገት ጠንካራ መሰረት መጣሉን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰሞኑን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቀቂያ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት በሰጡት ሰፊ ማብራሪያ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
የመርሃ ግብሩ ስኬት በብዙ መልኩ የሚገለጽ ስለመሆኑ አንስተው የተቋማት የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ መጠናከር በተለይም ደግሞ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ለዘርፉ ስኬት ጥሩ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ በመነሳት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን መፍጠር የስትራቴጂው ቁልፍ መሰረታዊ ትልሞች መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይ የህዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋት ላይ ትልቅ ስራ የሚከናወን ሲሆን ይህም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰው ተኮር ሆኖ የዜጎችን ኑሮ እንዲያሻሽል ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስኬት ዘርፉ ቀጣይ ልማት እና እድገት ጠንካራ መሰረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮምፕዩተር ሳይንስና ኢንጂነሪግ ትምህርት መምህርና የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክተር ደረጄ ረጋሣ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዘርፉ እድገት ትልቅ መሰረተ ያኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የቴክኖሎጂ እሳቤ እንዲገባ ከማድረግ በዘለለ ህዝቡ ቴክኖሎጂን መጠቀም እንዲጀምር እድል የፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም ስትራቴጂው ከቴክኖሎጂ ልማት፣ እድገትና አጠቃቀም አንፃር የተቀመጠውን ግብና ዓላማ ያሳካ እንደነበር አመልክተው ከዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ ከኔትዎርክና ኢንተርኔት ልማት አንጻር የተሰሩ በጎ ስራዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ደግሞ በዘርፉ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ በመጠቀም ከቴክኖሎጂ ተደራሽነት ባሻገር በዘርፉ የላቀ ከፍታና እመርታን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም አዳዲስ ስልቶችና እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ጠቅሰው የሰው ኃይሉን በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት ማብቃት፣ ማዋሃድና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማስፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩተር ሳይንስና እንጂነሪንግ መምህር፣ የኤሌክትሪካልና ኃይድሮ ኤሌክትሮኒክስ የልህቀት ማእከል አስተባባሪ ከተማ አደሬ(ዶ/ር)፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ዘርፉን ለማሳደግ የሚያግዝ መሰረት የጣለ መሆኑን አመልክተዋል።
ስትራቴጂው በሰው ኃይል ልማት፣ በፋይናንስ ሴክተር አገልግሎት እንዲሻሻል፣ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነበር ብለዋል።
በትራንስፖርት፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በአንድ ማዕከል አገልግሎት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ስኬቶች መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እንዲሳካም የሰው ኃይል አቅም ማጎልበት፣ ቴክኖሎጂውን ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር ማቆራኘት እንዲሁም ፈጣንና ጥራት ያለው የዘርፉ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህ ሂደት የግሉ ዘርፍም አዎንታዊ ሚናውን በሚገባ መጫወት እንዳለበት አስገንዝበዋል።