በክልሉ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ፖሊስ የተቀናጀ ተግባር እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ፖሊስ የተቀናጀ ተግባር እያከናወነ ነው
ባሕር ዳር፤ ታኅሣሥ 14/2019(ኢዜአ)፡ - በአማራ ክልል ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል ፖሊስ ከሌሎች የፍትሕ ተቋማት ጋር የተቀናጀ ተግባር እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እና የፍትሕ ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች ሙስናና ብልሹ አሰራርን የመከላከል ቅንጅታዊ ስራ ላይ የመከረ መድረክ ዛሬ አካሂደዋል።
በመድረኩ የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የክልሉን ሕዝብና መንግስት ሃብት ከምዝበራና ከብልሹ አሰራር ለመታደግ የምርመራና የክስ ተግባር በቅንጅት እየተከናወነ ነው።
ፖሊስ በተደራጀ መረጃና ማስረጃ የተደገፈ ምርመራ የማካሄድ ሃላፊነት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ሌሎች የፍትሕ ተቋማት ደግሞ በምርመራ የተገኘውን ውጤት ተጠያቂነት እንዲሰፍን የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።
ይህንን የተቋማዊ ቅንጅታዊ አሰራር በማስፋት የተገኘውን አበረታች ውጤት ማጠናከር የሚያስችል ተግባር መቀጠሉን ተናግረዋል።
ፖሊስ እና አቃቢ ሕግ መዳረሻቸው ብልሹ አሰራርን መከላከልና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማስቻል ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ሃላፊ ብርሃኑ ጎሽም ናቸው።
የቅንጅት ስራው ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የተመዘበረ የመንግስትና የሕዝብ ሃብት እንዲመለስ እያስቻለ መሆኑን አንስተዋል።
ውስብስብ የሆነውን ሌብነትና ብልሹ አሰራር አስቀድሞ ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን የቅንጅት ስራው የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ከክልሉ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በኩል የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የሙስና ወንጀል ችሎት ምርመራ ዋና መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ዳምጤ ባየ፤ ባለፉት አምስት ወራት 556 መዝገቦች ላይ ምርመራ በማከናወን ከእነዚህ ውስጥ የ401 ተጣርቶ ጥፋተኛ በሆኑት ላይ ክስ እንዲመሰረት ለሚመለከተው አካል መላኩን ገልጸዋል።