ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የሀገር የህልውና ጉዳይ ሆኖ እየተነሳ ያለ የትውልድ ጥያቄ ነው

መቀሌ ፤ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የሀገር የህልውና ጉዳይ ሆኖ እየተነሳ ያለ የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በአንድ ወቅት የባህር በር ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በቅርብ እርቀት ላይ እያለች ምክንያቱ በውል በማይታወቅ መልኩ የባህር መውጫ መግቢያ ተነፍጓት የተቆለፈባት ሀገር ሆናለች።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልክአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ በቀይ ባህር ላይ መውጫና መግቢያ በር ማጣት የሌለባት በመሆኑ ጉዳዩ አሁን ላይ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ እየተነሳ ይገኛል።

የህግና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ያዕቆብ ኃይለማርያም (ዶ/ር) 'አሰብ የማን ናት' በሚለው መፅሃፋቸው የባህር በር ባለቤት በመሆን እና ባለመሆን መካከል ያለውን ልዩነት በስፋት አብራርተዋል።

የምጣኔ ሃብት ሊቁን ፖል ኮሊየርን በመጥቀስ 'የባህር በር ከሌለህ ገበያህ የጎረቤት ሃገር ብቻ ነው፤ የባህር በር ካለህ ግን ገበያህ መላው ዓለም ነው' የሚለውን ሃሳብ በማጣቀስ የባህር በር አልባ መሆን ያለውን ጉዳት አስረድተዋል።

አሁን ላይ ከ130 ሚሊየን በላይ የሚገመት ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት መዝለቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የሀገር የህልውና ጉዳይ ተደርጎ የሚነሳበት ምክንያት ግልጽና የማያሻማ ነው።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ በመቀሌ ያነጋገራቸው የማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ የሀገር የህልውና ጉዳይ ሆኖ እየተነሳ ያለ የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ገልጸዋል።

የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው መዘክር ገብረህይወት፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ተዘግቶባት ልትኖር የማትችል ሀገር መሆኗን አንስተው የባለቤትነት መብቷ ተከብሮ ምላሽ ሊሰጣት ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ግዙፍ ኢኮኖሚ፣ እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥር እና በቀይ ባህር አካባቢ ያለው ጅኦስትራቴጅክ አስፈላጊነት ታክሎበት ኢትዮጵያ ከባህሩ ተነጥላ ልትኖር የማይገባ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ምላሽ የሚፈልግ የትውልድ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ ሀደራ ባህታ፤ በቀጣናው የምጣኔ ሃብት ትስስርን ማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ የሚቻለው የአካባቢው አገራት በቀይ ባህር ላይ በጋራ መጠቀም ሲችሉ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ያገለለ የትኛውም የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ጥረትና ቀጣናዊ ትስስር ትርጉም የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከራሷ አልፎ ቀጣናዊ ሰላምና ልማትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ምላሽ ሊያገኝ ግድ ይላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም