ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ለማፋጠን ቁልፍ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ለማፋጠን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን በይፋ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎቹ ባቀረቡት ማብራሪያ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ የዜጎችን የዲጂታል ክህሎት ማሳደግ፣ የመንግስት ገቢን መጨመርና የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ሙሉቀን ቀሬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ በ2030 ስትራቴጂው መሠረት በሀገሪቱ የዲጂታል ንቃተ ህሊናን ለማሳደግ ግልጽ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 70 በመቶው የዲጂታል ዕውቀት እንዲኖረው እንደሚደረግ ጠቁመው፤ በተለይ 80 በመቶ የሚሆኑት የመንግሥት ሠራተኞች የዲጂታል ክህሎት ባለቤት ከማድረግ ባሻገር 10 ሚሊየን ዜጎች ቀጥተኛ የዲጂታል ሥልጠና እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማፋጠን አምስት ሺህ አዳዲስ ስታርታፖችን ወደ ሥራ ማስገባትና በዘርፉ ለአንድ ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ መያዙን ጠቅሰዋል።

ይህም የዲጂታል ዘርፉ በ2030 ለሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት የሚኖረው አስተዋጽኦ 12 በመቶ እንዲደርስ እንደሚያስችልም ተናግረዋል።


 

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ዳዊት ውብሸት በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የዲጂታል ሽግግሩ በመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ላይ ያመጣው ውጤት ተስፋ ሰጪ ነው።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ታክስ የመሰብሰብ አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደጉን ተናግረው፤ በአሁኑ ወቅት 58 ሺህ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በዲጂታል ሥርዓት እያሳወቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በ2030 ስትራቴጂ አማካኝነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተቀናጀ የዲጂታል ሥርዓት በመገንባት የታክስ አሰባሰቡን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ይድነቃቸው ወርቁ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የንግድ ስርዓቱን ማዘመን የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ይከናወናሉ።

እንደ ሀገር በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ያሉ አሰራሮችን ዲጂታል በማድረግ ዘርፉ ለኢኮኖሚ ያለውን ፋይዳ ይበልጥ እንዲጎለብት እንደሚደረግም አብራርተዋል።

በሚቀጥሉት ዓመታት የሚከናወነው ንግድ መልኩ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀየርና በአነስተኛ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች በዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የንግድ ስራ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም