የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ ነው
አዳማ፤ ታህሳስ 14/2018 (ኢዜአ)፡-የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ከዩ.ኤን. ውሜን (UN WOMEN) እና አክሽን ኤይድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 4ኛው ሀገር አቀፍ ሴቶችን በኢኮኖሚ የማብቃት ፎረም በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት የሴቶችን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ያለባቸውን ጫና ለመቀነስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።
ኢኮኖሚያዊ አቅማቸው የተሻለ የሆኑ ሴቶች ከጥገኝነት የተላቀቁና በራሳቸው የመወሰን አቅማቸውም ላቅ ያለ መሆኑን አንስተዋል።
የዘላቂ ልማት ግቦች አጀንዳ ለማሳካትም የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመው፣ በሁሉም ዘርፎች ሴቶችን ማበረታታትና መብታቸውን ማስከበር ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አክለዋል።
እንዲሁም ከግብርና ኢኒሼቲቭ ሥራዎች ባሻገር በኢንዱስትሪና በሌሎች መስኮች የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ፎረሙ ሴቶችን በኢኮኖሚ ከማብቃት ጋር ተያይዞ ለቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት በመሆኑ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድጉ ተግባራት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ለማጠናከር እድል ይፈጥራል ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የዩ.ኤን ውመን (UN WOMEN) የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሻድራክ ዱሳቤ በበኩላቸው ሴቶችን በሁለንተናዊ መልኩ ማብቃትና ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሴቶች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ለማጎልበት የሁሉም አካላት ትብብርና ቅንጅት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ፎረሙ የሴቶች ድምጽ በመሆን ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተለይ የመንግስት አመራር አካላት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ ሀብት በማሰባሰብ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ድርጅቱ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።