ቀጥታ፡

ልዩነቶች በሀገር በቀል እሴቶች መፈታት አለባቸው የሚለው የመደመር መንግሥት ዕሳቤ ውጤት እያስመዘገበ  ነው 

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነቶች በሀገር በቀል እሴቶች መፈታት አለባቸው የሚለው የመደመር መንግሥት ዕሳቤ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመደመር መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚል ግልጽ አቋም አለው፡፡

ኢትዮጵያውያን ሰላምን የሚያመጡበት ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት የቆየ ሀገር በቀል እውቀት፣ ልምድና እሴት አላቸው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ ለሰላም ግንባታ መሰረት የሚጥሉ ባህላዊ እሴቶች እንዳሉ በመጥቀስ፤ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካና ማህበራዊ እሴቶች ማደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ዜጎች በሰዎች መካከል መልካም መስተጋብር የሚፈጥሩበት፣ አንድነትን የሚያጎለብቱበት ከየትኛውም ሀገር ያልተቀዳ ከማህበረሰቡ የፈለቀ የዳበረ ልምድ አላቸው ብለዋል፡፡

ከዚህም በመነሳት የመደመር መንግሥት ሀገር በቀል እውቀትና ነባራዊ እሴቶችን ለሰላም ግንባታ ማዋል ይገባል የሚል እምነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የመደመር መንግሥት ለሰላም በራችን ክፍት፤ እጃችን የተዘረጋ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምን የገለጹት ቢቂላ (ዶ/ር)፤ የሰላምን መንገድ መርጠው ለውይይት የሚመጡ አካላትን ብዙ ርቀት ተጉዞ ይቀበላል ብለዋል፡፡

በባዳና ባንዳ ተልዕኮ የዜጎችን ሰላም ለማናጋት ጥረት ከሚያደርጉ አካላት ጋር ሁሉ የመጭውን ትውልድ ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ ለመነጋገር ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዜጎችን አብሮ የመኖር እሴት ለመሸርሸር የሚሰሩ አካላት እንዳሉ ገልጸው፤ አዎንታዊ ሰላም ለመገንባት የተዘረጋውን እጅ መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የመደመር መንግሥት ከማህበረሰቡ የተቀዳውን ሀገር በቀል እሴት ወደ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቀየር ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው የሚል ጽኑ አቋም መያዙን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሰላማዊ መንገድ የሰለጠነ የሀሳብ ልዕልናን ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚያስችል ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም