ቀጥታ፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 14/2018 (ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የቀረበለትን የተሻሻለውን የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንታይን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ረቂቅ አዋጁም በሰብል ላይ የሚከሰትን የዕፅዋት ተባይ በቅድመ መከላከል የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የምርት ብክነትን በመቀነስ የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል እንደሚረዳ ገልጸዋል።

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በዕፅዋትና ብዝኅ ሕይወት ሰፊ ጸጋ ቢኖራትም የተፈጥሮ ሃብቷን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል  የሕግ ማዕቀፍ አልነበረም። ይህም ማዕቀፉ ኋላ ቀር የሆነና ለቁጥጥር አመቺ ባለመሆኑ አዋጁን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።

ረቂቅ አዋጁ በዕፅዋት ላይ የሚከሰት ተባይና መጤ አረም ምክንያት በግብርና ምርታማነት ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ በጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ለመከላከል እንደሚያግዝ አስረድተዋል።

የዕጽዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅም የዓለም አቀፍ የዕፅዋት ጥበቃ ስምምነትን መነሻ በማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያ ለዕጽዋት ሀብቶቿ ተገቢውን እንክብካቤ በመስጠት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ አቅም መፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በዕፅዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅ ላይ ሃሳብና አስተያየት በመስጠት ረቂቅ አዋጁን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም