ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በገቢ ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት እያስቻለ ነው 

አዲስ አበባ ፤ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦በመደመር መንግሥት ዕይታ የተከናወነው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በሀገር ውስጥ ገቢ እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት እያስቻለ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማካሄድ እና ብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ በመንደፍ እመርታዊ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ትገኛለች።

በዚህ ተግባርም የኢትዮጵያ ዓመታዊ የገቢ አሰባሰብ በየዓመቱ ቀጣይነት ያለው ዕድገት እያሳየ የሚገኝ ሲሆን ለአብነትም በ2015 ዓ.ም 442 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር፣ በ2016 ዓ.ም 512 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ፣ በ2017 ዓ.ም 615 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መገኘቱን መጥቀስ ይቻላል።

መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ እና የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጥ፣ በጉምሩክ ቀረጥና በሀገር ውስጥ ታክስ አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ ገቢ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል።

በዚህም ምክንያት በ2018 የሀገሪቱ ዓመታዊ የገቢ ዕቅድ ወደ 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር አካባቢ ከፍ እንዲል መደረጉም ይታወቃል።

የገቢዎች ሚኒስትር ዓይናለም ንጉሴ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የመደመር መንግሥት እሳቤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ዘርፈ-ብዙ ፋይዳዎችን እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል። 

እሳቤው በሀገሪቷ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን ተግባራዊ ማድረጉን ጠቁመው፤  በዚህም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።

የሪፎርም ተግባራት ለገቢ ዕድገት ዋነኛ መሠረት መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በተለይም የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የገበያ ትስስርን በማጠናከርና የገቢ ግብርን የሚያሳልጥ የንግድ ፍሰት መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።

ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉና አምራች ዘርፉ ለሀገር ውስጥ የታክስ ገቢ ከፍተኛ ድርሻ እንዲያበረክት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ 

የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ዘመናዊና ፈጣን እንዲሆን በማድረግ ረገድ እሳቤው ቁልፍ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል። 

የመደመር መንግሥት ዋነኛ ግብ ሀገር በቀል  ኢኮኖሚን መገንባት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ጠንካራ የገቢ ግብር እንዲኖር የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለዚህም የኢኮኖሚ ሥርዓቱ ለግብር አሰባሰብ ምቹ እንዲሆን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች በስፋት እየተተገበሩ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ትልልቅ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች እመርታዊ ለውጥ ሲያስመዘግቡ የሚመነጨው ገቢ ለሀገር ልማትና ለኢንቨስትመንት ትልቅ ድርሻ እንዲያበረክት በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

 ከእነዚህ ዘርፎች የሚመነጨው ገቢ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ዋስትና እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም