በአፍሪካ ዋንጫ ትኩረት የሳቡ ወጣት ተጫዋቾች - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ዋንጫ ትኩረት የሳቡ ወጣት ተጫዋቾች
የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ እና አንጋፋ ተጫዋቾች የሚታዩበት መድረክ ብቻ አይደለም። እምቅ ችሎታ እና ብሩህ ተስፋ ያላቸው ወጣት ተጫዎቾች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበትም ጭምር ነው።
በተለያዩ የአፍሪካ ዋንጫዎች ደምቀው የታዩ የአፍሪካ ወጣት ተጫዋቾችን ለመመልከት ተችሏል።
ጋናዊው አቢዲ ፔሌ፣ የናይጄሪያው ንዋንኮ ካኑ፣ ካሜሮናዊው ሳሙኤል ኤቶ፣ የግብጹ ሆሳም ሚዶ፣ የዛምቢያው ካሉሻ ቡዋሊ፣ ኮትዲቯራዊው ዲዲየር ድሮግባ እና የጋቦኑ ፒዬር-ኤሜሪክ ኦቦሚያንግ በወጣትነት እድሜያቸው በአፍሪካ ዋንጫው ተሳትፎ በማድረግ በቀሪ እግር ኳስ ህይወታቸው ስኬታማ ከሆኑ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳሉ።
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ይገኛል።
በአፍሪካ ዋንጫው ጎልተው ይታያሉ የተባሉ ተጫዋቾችን እንመልከት።
- ቢላል ኤል ካኑስ (ሞሮኮ)
ኤል ካኑስ በአውሮፓ ከሚጫወቱ የአፍሪካ ተስፈኛ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው። በአሁኑ ሰዓት ከሌይስተር ሲቲ በውሰት ወደ ስቱትጋርት አቅንቶ እየተጫወተ ይገኛል።
በቤልጂየም የተወለደው የ21 ዓመቱ ተጫዋች ለአውሮፓዊቷ ሀገር በታዳጊ ብሄራዊ ቡድኖች በመሰለፍ ከእ.አ.አ 2022 አንስቶ ለሞሮኮ ዋና ቡድን እየተጫወተ ይገኛል።
የአጥቂ አማካይ ተጫዋቹ እ.አ.አ በ2022 በኳታር በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ሞሮኮ ከክሮሺያ ጋር ባደረገችው የደረጃ ጨዋታ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለሀገሩ አድርጓል።
ከዛ ጊዜ አንስቶ ለሞሮኮ 26 ጨዋታዎችን አድርጎ ሁለት ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። በውስን ቦታዎች እና በጠባብ ክፍቶች መሐል ያለው የፈጠራ አቅም ተጫዋቹ አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል።
- ላሚን ካማራ (ሴኔጋል)
የ21 ላሚን ካማራ የሴኔጋልን ማልያ ለመጀመሪያ ጊዜ የለበሰው እ.አ.አ በ2022 በአልጄሪያ አስተናጋጅነት በተካሄደው ሰባተኛው የአፍሪካ ሀገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ላይ ነው። የሀገር ውስጥ ሊግ ተጫዋቾች ብቻ በሚጫወቱበት ውድድር ከሀገሩ ዋንጫ አንስቷል።
በወቅቱ በሩብ ፍጻሜው ሞሪታኒያ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠራት ጎል ቡድኑ ለግማሽ ፍጻሜ እንዲያልፍ አስችሎታል። ከዛ ወቅት አንስቶ ለሴኔጋል 34 ጨዋታዎች አድርጎ ስድስት ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።
እ.አ.አ በ2024 ከሜትዝ ወደ ሞናኮ በማቅናት እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን በ38 ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ለሴኔጋል ዋናው ቡድን በመደበኛነት እየተሰለፈ የሚገኘው ካማራ ከአማካይ ክፍል በመነሳት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል የሚያደርጋቸው ፈጣን ሩጫዎች እና የሚፈጥራቸው የግብ እድሎች አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል።
- ካርሎስ ባሌባ (ካሜሮን)
ካርሎስ ባሌባ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለብራይተን ኤንድ ሆቭ አልቢየን የሚጫወት ነው። ተጫዋቹ በአማካይ እና በተከላካይ አማካይ ስፍራ መጫወት የሚችል ነው።
በካሜሮን ዱዋላ የተወለደው ባሌባ አባቱ ለደቡብ አፍሪካ እና ካሜሮን ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል። እ.አ.አ በ2023 ከፈረንሳዩ ሊል ወደ ብራይተን በማምራት ድንቅ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል።
ባሌባ ለካሜሮን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው እ.አ.አ በ2024 ሀገሩ ከኬፕቨርዴ ጋር ባደረገችው የዓለም ማጣሪያ ጨዋታ ላይ ነው። ከዛ ጊዜ ጀምሮ ለብሄራዊ ቡድኑ 11 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ምንም ጎል አላስቆጠረም።
ታታሪነት፣ ኳስ በብቃት ማንከባለል እና ኳስን ማቀበል የተጫዋቹ መገለጫዎች ናቸው። በሜዳው ውስጥ ከሳጥን እስከ ሳጥን በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከፖል ፓግባ፣ ቲያጎ አልካንታራ እና ኬቨን ደ ብሮይን ጋር የሚያነጻጽሩትም አሉ።
- ኦማር ዲያኪቴ (ኮትዲቭዋር)
የአጥቂ መስመር ተሰላፊው ኦማር ዲያኪቴ በአፍሪካ ዋንጫው ከሚጠበቁ ወጣት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
የ21 ዓመቱ ተጫዋች በአሁኑ ከፈረንሳዩ ሬሚስ በውሰት ወደ ቤልጂየሙ ሴርክል ብሩዥ በማምራት እየተጫወተ ይገኛል።
ዲያኪቴ ለሀገሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታውን ያደረገው እ.አ.አ በ2023 ኮትዲቭዋር ከሌሴቶ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ላይ ሲሆን ለብሄራዊ ቡድኑ ባደረጋቸው 23 ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
እ.አ.አ በ2023 በኮትዲቭዋር አስተጋጅነት በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫም ተሳትፎ አድርጓል።
የዲያኪቴ የአጨራረስ ብቃት እና የቦታ አያያዙ ለተከላካዮች ፈተና ነው።
- ትራቪስ ሙታባያ (ዩጋንዳ)
የ20 ዓመቱ ሙታባያ በምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ ተስፋ ከተጣለባቸው ባለ ክህሎት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።
የአማካይ መስመር ተሰላፊው ከፈረንሳዩ ቦርዶ እ.አ.አ በ2025 ወደ ቱኒዚያው ስፋክሲያን በማምራት እየተጫወተ ይገኛል።
በዩጋንዳ ታዳጊ ብሄራዊ ቡድኖች ላይ ድንቅ ብቃቱን ካሳየ በኋላ ከአራት ዓመት በፊት በ16 ዓመቱ በዋናው ቡድን እንዲጫወት ጥሪ ቀርቦለታል። የመጀመሪያ ጨዋታውንም ዩጋንዳ ከታንዛንያ ባደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ አከናውኗል።
ለሀገሩ እስከ አሁን ባደረጋቸው 24 ጨዋታዎችን ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል። በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ተሳትፎውን የሚያደርገው የ20 ዓመቱ ተጫዋች የመፍጠር አቅሙ፣ የስራ ታታሪነት እና ኳስ የማንከባለል ክህሎቱ አድናቆት እንዲቸረው አድርጓል።
የታንዛንያው ኬልቪን ጆን፣ የዛምቢያ ሚጉዌል ቻዋ፣ የሴኔጋሉ ኢብራሂም ምባዬ፣ የሴኔጋሉ ፓፔ ማታር ሳር እና የሞሮኮው ኤሊስ ቤን ሴግሂር ሌሎች አይን ያረፈባቸው ወጣት ተጫዋቾች ናቸው።