ቀጥታ፡

የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ ጸንቶ የቆየ አጋርነት አላቸው-ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እና ለረጅም ጊዜ ፀንቶ የቆየ አጋርነት አላቸው ሲሉ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።

በአሜሪካ የአፍሪካ ህብረት ልዑክ ኃላፊ አምባሳደር ኮንስታንሲያ አዴሊና ጋስፓራስ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በነጩ ቤተ መንግስት (ዋይት ሃውስ) በተካሄደ ስነ ስርዓት የአምባሳደር ኮንስታንሲያን ሹመት በይፋ ተቀብለዋል።

አምባሳደሯ በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው በአሜሪካ የአፍሪካ ህብረት ልዑክ ቢሮ ስራቸውን በይፋ ጀምረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ የአምባሳደር ኮንስታንሲያ የልዑኩ መሪ ሆኖ መመረጥ በጋራ የኢኮኖሚ እድሎች፣ በሉዓላዊ አመራር ሰጪነት እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት ላይ የተመሰረተውን የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ ጽኑ አጋርነት የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ በአፍሪካ ሰላም፣ ብልጽግና እና መረጋጋትን ማረጋገጥን ዋና ማዕከል ያደረገ ጠንካራ የአጋርነት ስራ እያከናወኑ እንደሚገኝ የህብረቱ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም