ከድምጽ ማዳመጫ (ኤርፎን) አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የጆሮ ጤናን ይጎዳል የሚባለው የከፍተኛ ድምጽ ልኬት ስንት ነው? - ኢዜአ አማርኛ
ከድምጽ ማዳመጫ (ኤርፎን) አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የጆሮ ጤናን ይጎዳል የሚባለው የከፍተኛ ድምጽ ልኬት ስንት ነው?
ለጆሮ ህመም አጋላጭ የሆኑ መንስዔዎችን በመለየት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን የአንገት በላይ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ካሳዬ አሽኔ ይመክራሉ።
• የጆሮ ጤናን ይጎዳል የሚባለው የከፍተኛ ድምጽ ልኬት ስንት ነው?
ከፍተኛ የሆነ ድምጽ የጆሮ ጤናን ይጎዳል ያሉት የሕክምና ባለሙያው፤ ከፍተኛ ድምጽ ሲባልም እንደ አካባቢው እና እንደ ሁኔታው የሚወሰን ሆኖ (ለምሳሌ ቤተመጻሕፍት ውስጥ፣ ገበያ ውስጥ፣ መኖሪያ ቤት ውስጥ የድምጽ ብክለት መጠኑ ስለሚለያይ) በአማካይ ከ90 ዴሲ ሜይል በላይ የሆነ ማለት ነው ይላሉ።
በአማካይ ከ90 ዴሲ ሜይል በላይ የሆነ ድምጽ ከ8 ሠዓት በላይ ለሆነ ጊዜ ለጆሮ የሚደርሰው ከሆነ በሂደት የጤና ችግር እንደሚያስከትልም አስገንዝበዋል።
ስለዚህ ጆሮ ጤናው ሳይታወክ በአግባቡ ማስተናገድ ከሚችለው በላይ የሆነ ድምጽ ሲደጋገምበት በውስጠኛው የጆሮ ክፍል የሚገኙ የድምጽ መቀበያ እና ማስተላለፊ ነርቮች በሂደት በከፍተኛ የድምጽ ብክለት ምክንያት ሊጎዱ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ድምጽ የጆሮ ታንቡርንም ሊጎዳ እንደሚችል ጠቁመው፤ በአብዛኛው ግን ውስጠኛውን የጆሮ ክፍል ይጎዳል፤ ድምጽን ተሸክሞ ወደ አንጎል የሚሄደውን የነርቭ ክፍል ነው የሚጎዳው ሲሉ አስረድተዋል።
• ከድምጽ ማዳመጫ (ኤርፎን) አጠቃቀም ጋር በተያያዘ
በኤርፎንም ሆነ በቀጥታ ወደ ጆሮ የሚደርሱ ድምጾች ሊመጠኑ ይገባል ያሉት የሕክምና ባለሙያው፤ ይህ ካልሆነ ግን የመስማት መጠን በሂደት እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በሌላ በኩል ኤርፎን ለረጅም ጊዜ በጆሮ ላይ ሲቀመጥ፤ የጆሮ የውጨኛው ክፍል የመፈግፈግ (መላላጥ) ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል ጠቁመዋል። ይህም ወደ ማመርቀዝ (ኢንፌክሽን) አድጎ ጉዳት እንዳያስከትል ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ይላሉ።
እንዲሁም ኤርፎኑ በጆሮ ቀዳዳ (ካናል) ላይ ለረጅም ጊዜ ሲቀመጥ ከውስጥ ወደ ውጭ መውጣት ያለበት ኩክ እንዳይወጣ በመግፋት ድምጽ በሚፈለገው ልክ እንዳይተላለፍ በማድረግ የመስማት ዕድልን ሊቀንሰው ይችላል ብለዋል።
በተጨማሪም ኤርፎን መዋዋስም ለኢንፌክሽን የመጋለጥ ዕድልን እንደሚጨምር አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የኤርፎን አጠቃቀም ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገበት በውጨኛው እና በውስጠኛው የጆሮ ክፍል ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ገልጸዋል።