የምስራቅ አፍሪካዎቹ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካዎቹ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018 (ኢዜአ)፦ በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ሶስት እና አራት የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ።
በምድብ ሶስት ናይጄሪያ ከታንዛንያ ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ላይ በፌዝ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ናይጄሪያ እ.አ.አ በ1980 ባዘጋጀችው 12ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በምድብ ተገናኝተው አዘጋጇ ሀገር 3 ለ 1 አሸንፋለች።
የሶስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በውድድሩ ላይ 22ኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች። ታንዛንያ በአህጉራዊ መድረክ የመሳተፍ እድሉን ስታገኝ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
በዚሁ ምድብ ዩጋንዳ ከቱኒዚያ ምሽት አምስት ላይ በፕሪንስ ሙላይ አብደላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1962 ባዘጋጀችው ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በደረጃ ጨዋታ ተገናኝተው ቱኒዚያ 3 ለ 0 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ቱኒዚያ በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ ለ22ኛ ጊዜ ሲሆን እ.አ.አ በ2004 ራሷ ያዘጋጀችውን 24ኛ የአፍሪካ ዋንጫ አንስታለች።
በውድድሩ ላይ ለስምንተኛ ጊዜ የምትሳተፈው ዩጋንዳ በበኩሏ ትልቁ ውጤቷ እ.አ.አ በ1978 በጋና በተካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው።
ዩጋንዳ እና ታንዛንያ በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ከተጋጣሚዎቻቸው ይጠብቃቸዋል።
በተያያዘም የምድብ አራት ጨዋታዎችም ዛሬ ይካሄዳሉ።
የሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከቤኒን ጋር ከቀኑ 9 ሰዓት ከ30 ጋር በአል መዲና ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ ሲገናኙ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአፍሪካ ዋንጫ ለ19ኛ ጊዜ፣ ቤኒን ለአምስተኛ ጊዜ ይሳተፋሉ።
ቤኒን ትልቁ ውጤቷ እ.አ.አ በ2019 በግብጽ በተካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለሩብ ፍፃሜ ያለፈችበት አጋጣሚ ነው።
በዚሁ ምድብ ሴኔጋል ከቦትስዋና ምሽት 12 ሰዓት ላይ በታንጂየር ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሴኔጋል በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ የአሁኑ 18ኛ ጊዜ ሲሆን ቡድኑ የ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ነው። ቦትስዋና ከ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ሁለተኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።