ቀጥታ፡

አርሰናል እና ክሪስታል ፓላስ በካራባኦ ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ይጫወታሉ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 14/2018(ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ካራባኦ ዋንጫ የመጨረሻው የሩብ ፍጻሜ መርሃ ግብር በአርሰናል እና ክሪስታል ፓላስ መካከል ዛሬ ይደረጋል።

ጨዋታው ምሽት አምስት ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።

አርሰናል በአራተኛው ዙር ብራይተንን 2 ለ 0፣ ክሪስታል ፓላስ ሊቨርፑልን 3 ለ 0 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፈዋል።

ሁለቱ ቡድኖች እ.አ.አ 1992/93 በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው አርሰናል በደርሶ መልስ በማሸነፍ ለፍጻሜው ያለፈ ሲሆን ሼፍልድ ዌንስደይን በመርታት ዋንጫውን አንስቷል።

አርሰናል ከዛ ጊዜ አንስቶ የካራባኦ ዋንጫን አንስቶ አያውቅም። ቡድኑ በአጠቃላይ ሁለት ጊዜ ውድድሩን አሸንፏል።

ክሪስታል ፓላስ በካራባኦ ዋንጫ ትልቁ ውጤቱ በአራት አጋጣሚዎች ለግማሽ ፍጻሜ ያለፈባቸው ናቸው።

ቡድኖቹ ዘንድሮ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባደረጉት ጨዋታ አርሰናል 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከቼልሲ ጋር ይጫወታል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ባለፈው ሳምንት መደረግ የነበረበት ቢሆንም በመርሃ ግብር መደራረብ ምክንያት ወደዚህ ሳምንት መራዘሙ ይታወቃል።

ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ መርሃ ግብር በኒውካስትል ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ መካከል ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም