ቀጥታ፡

የመንግሥት ተቋማት ዕቅድ ሲያወጡና ሲተገብሩ  ከሰላም ግንባታ አንፃር የነበራቸውን ሚና መገምገም  አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦የመንግሥት ተቋማት ዕቅድ ሲያወጡና ሲተገብሩ በሥራዎቻቸው ከሰላም ግንባታ አንፃር የነበራቸውን ሚና መገምገም እንዳለባቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሰላም ሚኒስቴር ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች የህግ ማውጣት፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ሲያከናውኑ የሰላም አካቶ ትግበራን እውን ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሰላም ግንባታ የእያንዳንዱ ተቋም ኃላፊነት ነው፡፡

ሰላም የሁሉም ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን በመግለጽ፤ ሁሉም አካል ሰላምን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴው ዕቅድ አካል ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የሰላም ግንባታ በሁሉም ዕቅዶች፣ በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መካተት አለበት ያሉት ቢቂላ (ዶ/ር) ተቋማት ለአዎንታዊ ሰላም (Positive peace) ግንባታ አሻራቸውን ማስቀመጥ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡


 

ተቋማት ግጭትን መከላከልና ማስቀረት የሚያስችል የሰላም ዕቅድ የሥራቸው አካል መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በዚህም ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ የመንግሥት ተቋማት ዕቅድ ሲያወጡ፣ ሲተገብሩና ክትትል ሲያደርጉ  ከሰላም ግንባታ አንፃር የነበራቸውን ሚና መገምገም እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም