በላሊበላ የሚከበረው የገና በዓል በአማራ ክልል ለሚታየው የቱሪዝም መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
በላሊበላ የሚከበረው የገና በዓል በአማራ ክልል ለሚታየው የቱሪዝም መነቃቃት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ ታኅሣስ 13/2018 (ኢዜአ)፡- በላሊበላ ከተማ በድምቀት የሚከበረው የገና በዓል ለአማራ ክልል የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንዳለው የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
ላሊበላ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ከመሆኑ ባለፈ የገና በዓል በድምቀት ስለሚከበርበት በርካታ ቱሪስቶች በተለያዩ የመጓጓዣ አማራጮች ወደ ሥፍራው እንደሚመጡ የቢሮ ኃላፊ መልካሙ ፀጋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ቱሪስቱም የተቀናጀ የቱሪዝም አገልግሎትን መሰረት አድርጎ ስለሚመጣ ላሊበላን ብቻ ሳይሆን፤ ሌሎች መዳረሻዎችን አሥተሣሥሮ እንደሚጎበኝም ጠቁመዋል።
ይህም እንደ ክልል ያለውን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ያደርገዋል ነው ያሉት ኃላፊው።
ክልሉ በባህል፣ በቅርስ፣ በእንግዳ ተቀባይነትና በሌሎች ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ድንቅ ምድር መሆኑን ጠቁመው፤ ሕዝቡ በሚታወቅበት እንግዳ ተቀባይነት ባህሉ ለጎብኚዎች አቀባበል እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስትም በዓሉ በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር እና ለእንግዶቹም ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሳይ ወዳጆ በበኩላቸው፤ ከቱሪዝም ጋር የተሣሠረውን የከተማዋን ኢኮኖሚ በይበልጥ በማነቃቃት ረገድ የገና በዓል ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢኮኖሚው ከቱሪዝም ጋር መቆራኘቱን የተገነዘበው የከተማዋ ነዋሪም፤ የአካባቢውን ሰላም በማጽናት ለእንግዶች ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል ብለዋል።