በክልሉ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ሰላምን በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ሰላምን በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ጋምቤላ፤ ታህሳስ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ሰላምን በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በወቅታዊ የፀጥታና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ፤ በክልሉ ሰላምን ለማወክና ልማትን ለማደናቀፍ እኩይ አላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የፀጥታ ችግር እንዲከሰትና የልማት ስራዎች እንዲስተጓጎሉ ጥረት ማድረጋቸውን አንስተው በህዝቡና የጸጥታ ሃይሉ ትብብር የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥና ሰላምን በማጽናት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በክልሉ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅና ልማትን የማስቀጠል ስራ በልዩ ትኩረት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ጥረት ውስጥ የህዝቡ ትብብር አበረታች መሆኑን አንስተው በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የጥፋት ቡድኖችን እኩይ አላማ በማክሸፍ ለክልሉ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።