በምዕራብ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 300 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 300 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል
አምቦ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦በምዕራብ ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 300 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በዞኑ የቶኬ ኩታዬ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስራ በዞንና በወረዳ የስራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲሳ ሀይሉ እንዳሉት፤ በበጋ መስኖ ስንዴ 400 ሺህ ሔክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ።
በእስካሁኑ ሂደትም 320 ሺህ ሄክታር መሬት የማሳ ዝግጅት ተጠናቅቆ 300 ሺህ ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን ጠቅሰው አጠቃላይ ከሚለማው መሬትም 12 ነጥብ 6 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን ስኬታማ ለማድረግ ከባለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመውሰድ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር በተሻለ መልኩ ማቅረብ እንደተቻለና አርሶ አደሩ የግብርና ፓኬጆችን እንዲተገብርም ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን አመልክተዋል።
የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዋዬሳ አለሙ በበኩላቸው፤ በወረዳው የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴን በመተግበር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በወረዳው 20 ሺህ ሔክታር መሬት በስንዴ ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ10 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም የእቅዱ አካል የሆነው በወረዳው በኢመላ ዳዌ አጆ ቀበሌ 102 ሔክታር መሬት ላይ የስንዴ ዘር የመዝራት መርሃ ግብር መካሄዱን ገልጸው በልማት ስራውም 208 አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም የተሳተፉበት ነው ብለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው በዓመት ሶስት ጊዜ ማልማት እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
አርሶ አደር አራርሳ ዲልጋሳ እንዳሉት፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከጀመሩ ወዲህ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ አልፈው ገቢያቸው እያደገ ልጆቻቸውን በተሻለ ሁኔታ እያስተማሩ ነው።
በዚህ ዓመት ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም በመደራጀት ስንዴ መዝራታቸውን ገልጸው ከአንድ ሄክታር 35 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁም አመላክተዋል።
ሌላው የወረዳው አርሶ አደር ገመቹ ደንደና፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም በበጋ መስኖ ስንዴ እያለሙ መሆኑን ገልጸው በዚህም ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘንድሮም በወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አማካኝነት የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እና ትራክተር ቀርቦላቸው ስራውን በስፋት እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።