በካፋ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በካፋ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው
ቦንጋ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦በካፋ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ ያለመ ጉብኝት በካፋ ዞን ተደርጓል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ እንደገለፁት፤ ዞኑ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች መገኛ፣ የቱባ ባህልና የበርካታ እሴቶች ባለቤት ከመሆኑም ባለፈ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተከባብረውና ተዋደው የሚኖሩበት የሰላም ተምሳሌት ነው።
በዞኑ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎች፣ የካፋ ባዮስፌር፣ ፍልውሃና ሌሎች የጎብኚዎችን ቀልብ የሚይዙ የመስህብ ስፍራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት መሰረት በማድረግ እነዚህን ሀብቶች በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአንድ ወረዳ አንድ የለማ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኖር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ፓኬጅ እና ብራንድ ዝግጅት ዴስክ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ኦልጅራ፣ ኢትዮጵያን ምድረ ቀደምት ሀገር ከሚያስብላት አንዱ የቡና መገኛ መሆኗ ነው ብለዋል።
ይህንን ሀብት በደንብ በማስተዋወቅ ወደ ቱሪዝም ሀብትነት ለመቀየር ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው በቡና ልማት የሚታወቀውን የደቡብ የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢን ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር ለምለም አስራት በበኩላቸው፣ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በርካታ ጎብኚዎች አካባቢውን ለመጎብኘት ቢመጡም በቂና ምቹ ማረፊያ ባለመኖሩ የቆይታ ጊዜያቸው አጭር እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ደረጃቸውን የጠበቁ ማረፊያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።