ሀገር በቀል እውቀቶችን በአንድ ቋት በማሰባሰብ ለሀገር ልማት እንዲውሉ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር በቀል እውቀቶችን በአንድ ቋት በማሰባሰብ ለሀገር ልማት እንዲውሉ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሚገኙ እምቅ ሀገር በቀል እውቀቶችን በአንድ ማዕከላዊ ቋት በማሰባሰብ ለሀገር ልማትና ለፖሊሲ ግብዓት ለማዋል የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
መንግሥት የሀገር በቀል እውቀቶችን ለሀገራዊ ብልጽግና እና ለማንነት ግንባታ ያላቸውን ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ በመገንዘብ፣ እነዚህ እውቀቶች ተጠብቀው እንዲቆዩና ለዘመናዊው የልማት ጉዞ ግብዓት እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ያካበተቻቸው በርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች ቢኖሯትም፣ እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደራጀ መልኩ ባለመያዛቸው በሚፈለገው መጠን ጥቅም ላይ ሳይውሉ መቆየታቸውም ይገለፃል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየአካባቢያቸው የሚገኙ ጥበቦችን መለየትና መሰነድ በሚችሉባቸው ዘዴዎች ላይ ያተኮረ ስልጠና እያካሄደ ይገኛል።
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሽኔ እንደገለጹት፣ አሁን የተዘረጋው አሰራር እነዚህን የተበታተኑ እውቀቶች በአንድ ቋት በማሰባሰብ ለትምህርት ስርዓቱ፣ ለምርምርና ለፖሊሲ ግብዓትነት ለማዋል ያስችላል።
ይህም ሀገራዊ ችግሮችን በሀገር በቀል መፍትሄዎች ለመፍታት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የኮሚኒቲ ኢንጌጅመንትና ሀገር በቀል እውቀት ዴስክ ሀላፊ ሰላም አለሙ በበኩላቸው፤ ሀገር በቀል እውቀቶቹን ከመሰነድ ባለፈ በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች እምቅ ሀገር በቀል እውቀቶች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሚሪጊሳ ካባ ናቸው።
እነዚህ ሀገር በቀል እውቀቶችን በመሰነድ ለትምህርት ስርዓት፣ ለፖለሲ አቅጣጫ፣ ለልማትና ሌሎች ስራዎች እንዲውሉ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሰቲ የአንኮበር የእጽዋትና ሀገር በቀል እውቀት ልማት ማእከል አስተባባሪ አማረ አያሌው (ዶ/ር) እና በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የሀገር በቀል እውቀት ማእከል አስተባባሪ ያስሚን መሀመድ፤ በየአካባቢው ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን የማሰባሰብ፣ በቴክኖሎጂ የማስደገፍና በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም እነዚህን በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደራጀ መልኩ ለማጠናከር ስራዎች መጀመራቸው ውጤታማ ለመሆን ያስችላልም ብለዋል።