በሚቀጥሉት አስር ቀናት በተወሰኑ የመኸር ሰብል አብቃይ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ይችላል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በተወሰኑ የመኸር ሰብል አብቃይ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ይችላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት በተወሰኑ የመኸር ሰብል አብቃይ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ሊከሰት ከሚችል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታዎች የተሻለ ገጽታ እንደሚኖረው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።
በአብዛኛዎቹ የመኸር ሰብል አብቃይ በሆኑ የሰብል ስብሰባና ድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራት እየተከናወነ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ ደረቃማ እርጥበት ሁኔታ እንደሚጠበቅ ገልጿል።
በሚቀጥሉት አስር ቀናትም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ መካከለኛና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳይ ሊያስከትል እንደሚችል አስገንዝቧል።
ህብረተሰቡም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፏል።
በዚህም በደረቅ ቀናት የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
በተቀሩት የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተስተዋለው ደረቃማ የአየር ሁኔታም የደረሰ ሰብል ለመሰብሰብና ለድኅረ ሰብል ስብሰባ ሥራ አመቺ የአየር ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቋል።
ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ የሚነፍሰው ደረቅና ቀዝቃዛ የአየር ጠባይ እንደሚቀጥልም አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የበጋው ደረቅ፣ ጸሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚስተዋል ሲሆን የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚስተዋልም አስገንዝቧል።
በዚህም በሰሜን፣ ምስራቅ፣ መካከለኛውና ደቡብ ደጋማ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ከአምስት ዲግሪ ሴልሺየስ በታች እንደሚሆን የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ ብሏል።
ባለፉት ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከነበረው የደመና ሽፋን መጨመር ጋር ተያይዞ በደጋማ አካባቢዎች ላይ የነበረው ቅዝቃዜ እንዲቀንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ገልጿል፡፡