ቀጥታ፡

በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች የማህበረሰቡን ኑሮ የሚለውጡ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

ጂንካ ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ኑሮ የሚለውጡ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የመቶ ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም የተገመገመበት መድረክ ዛሬ በጂንካ ከተማ ተካሂዷል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የቆላማ አካባቢ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቲዮስ ጋርሾ እንደገለጹት፤ በክልሉ በመቶ ቀናት ዕቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች አንዱ በቆላማ አካባቢዎች የማህበረሰቡን ኑሮ የሚለውጡ ተግባራትን ማከናወን ነው።

ለዚህም በክልሉ ተረጂነትን ወደ ዜሮ በማውረድ የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የተቀናጀ የመስኖ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በመስኖ ልማቱ የአርብቶ አደሩ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ ይህንን ለማጠናከርም በነዳጅ የሚሰሩ የመስኖ አውታሮችን ወደ ሶላር እና ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር ሥራ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

ዘንድሮም በኛንጋቶም ወረዳ የሚገኙ የአይፓ እና ናፑቱኮይት መስኖ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ ለማሸጋገር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በቀጣይም የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጡና የገቢ አማራጭ በመሆን ኑሮን የሚያሻሽሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ማቲዎስ ተናግረዋል።

በተለይ የአርብቶ አደሩ እንስሳት ለድርቅ ያለውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ የመኖ ልማት ሥራዎች በትኩረት ከሚከናወኑ ተግባራት አንዱና ዋንኛው መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ማቲዮስ ገለጻ፤ በክልሉ በ90 ቀናት ውስጥ ከ90 በላይ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ተግባራት ለማሰማራት ታቅዷል።

በእስካሁንም 25 ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ የገቢ ማስገኛዎች ተደራጅተው በቅርቡ ወደ ሥራ እንደገቡ የገለጹት ኃላፊው፣ ቀሪዎቹን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ኢንተርፕራይዞቹን ውጤታማ ለማድረግም ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ለማመቻቸት ቢሮው ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም