ቀጥታ፡

የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ወደ ትልልቅ ፋብሪካዎች እንዲያድጉ እየተሰራ ነው

ሮቤ ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን በማጠናከር ወደ ትልልቅ ፋብሪካዎች እንዲያድጉ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ገለጸ። 

የክልሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በሮቤ ከተማ የጎጆ ኢንዱስትሪን ጨምሮ በተለያየ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል። 

የኦሮሚያ ክልል ስራ እድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የወጣቱን የስራ ፈጠራ አቅም የሚያጎለብቱ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ትልልቅ ፋብሪካዎች ለማሳደግ የተለያየ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው። 


 

የጎጆ ኢንዱስትሪዎች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች የበለጠ እንዲጠናከሩ የብድር፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲመቻችላቸው እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። 

እንዲሁም በዘርፉ ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶች አስፈላጊ ማሽኖችን በሊዝ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። 

ኢንጂነር ኤባ እንዳሉት፤ በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት የጎጆ ኢንዱስትሪን ጨምሮ በተለያየ የስራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ከ700 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ተመቻችቶላቸዋል። 


 

በሮቤ ከተማ በዘርፉ በተሰማሩ ወጣቶች እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት በተሞክሮነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመው መንግስት ከዘርፉ ከሚጠብቀው ግብ አንፃር ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል። 

በተለይም የጎጆ ኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማጠናከር በርካታ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ወደ ትልልቅ ፋብሪካዎች እንዲያድጉ ድጋፍና ክትትሉ ይጠናከራል ብለዋል። 

የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ዲኖ አሚን በበኩላቸው፤ በከተማው የወጣቱን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በከተማዋ ባለፉት አምስት ወራት በተለያዩ ዘርፎች የሥራ ዕድል ለተፈጠረላቸው ከ6 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መመቻቸቱን በማሳያነት አንስተዋል። 

በቀጣይም በጎጆ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ስራቸውን እንዲያስፋፉ የሚያግዙ የግብዓትና የፋይናንስ ድጋፎች እንዲደረግላቸውም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ነው ያሉት። 


 

በጎጆ ኢንዱስሪዎች የስራ እድል ከተፈጠረላቸው የከተማዋ ወጣቶች መካከል ደረጄ ወርቅነህ፣ ማህበራቸው ከመንግስት በተመቻቸለት 2 ሚሊዮን ብር ብድር በመኖ ማቀነባበር ዘርፍ ወደ ሥራ በመግባት ውጤታማ መሆኑን ገልጿል።

በተሰማሩበት የስራ ዘርፍም ከራሳቸው አልፈው 27 ለሚሆኑ ሌሎች የአካባቢያቸው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም አንስቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም