የኢትዮጵያ ዲጂታል ዘመን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዲጂታል ዘመን
የኢትዮጵያ ዲጂታል ዘመን
የዲጂታል ቴክኖሎጂ የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በወቅቱ የኤሌክትሮኒክ መሳሪዎችን ተጥቅሞ መረጃን በመተንተን እና መረጃን እንደ ልዩ ገጽታ በመጠቀም እና መለያ ቁጥር (ኮድ) በመስጠት አገልግሎት ላይ ይውል ነበር።
ከዛ ጊዜ በኋላ በርካታ የኮምፒዩተር ፕሮግራሞች እና ማሽኖች ተፈብርከው ጥቅም ላይ መዋል ጀምረዋል።
እ.አ.አ በ1946 በአሜሪካ የፔንሲሊቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ጥቅል አገልግሎት የሚሰጥ የመጀመሪያውን የኤሌክትሮኒክ ዲጂታል ኮምፒዩተር በመስራት የዲጂታል ዘመን ጅማሮን አበሰረ።
ከእ.አ.አ 1943 እስከ 45 ባለው ጊዜ ውስጥ የተሰራው ይህ ኮምፒዩተር ባለቤቶች ጆን ማውችሊ እና ጄ ፕሬስፐርት ኤከርት ናቸው።
በ150 ኪሎ ዋት ኃይል የሚሰራው ኮምፒዩተር በሴኮንዶች ውስጥ በርካታ ስራዎችን ያከናውን ነበር። ኮምፒውተሩ በወቅቱ በነበሩ ባለሙያዎች ማርሽ ቀያሪ እና መሰረት ጣይ የሚል ስያሜ አግኝቷል።
የዘመናዊ የዲጂታል ስርዓቶች ምሰሶ ነው የሚባለው ኢንተርኔት የተጀመረው እ.አ.አ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ነበር። “አርፓኔት” የተሰኘ የአሜሪካ የጥናት ፕሮጀክት ኮምፒዩተሮችን ዘመኑ ከደረሰበት የኔትወርክ ስርዓቶች ጋር በማገናኘት የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል።
እንግሊዛዊው የኮምፒዩተር ሳይንቲስት ቲም በርነርስ ሊ እ.አ.አ 1969 “ወርልድ ዋይድ ዌብ” (WWW) በመፍጠር ትስስርን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ አሸጋግሯል። ድረ ገጾችን በመፍጠር እና በህዝብ ደረጃ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲሰፋ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከኮምፒዩተር መሰራት ተነስቶ ወደ ዓለም አቀፍ የትስስር መሰረተ ልማትነት የተቀየረ ሲሆን በየዕለት ተዕለት የሰዎች ኑሮ፣ማህበራዊ መስተጋብር፣ ንግድ እና የመንግስታት አሰራር ላይ ከፍተኛ ለውጥ ከማምጣት ባለፈ ዘርፎች በቴክኖሎጂ እንዲቃኙ አድርጓል።
ዓለም ላይ አሁን ካለው ህዝብ 73 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው። የዲጂታል ኢኮኖሚ የዓለምን ጥቅል ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) የ15 በመቶ ድርሻን እንደሚያግዝ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። ሞባይል ለኢንተርኔት መስፋፋት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።
ሀገራት እ.አ.አ 2025 በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ክላውድ ኮምፒዩቲንግ፣ ኔትወርኪንግ እና ለሌሎች ትራንስፎርሜሽ ስራዎች ያወጡት ኢንቨስትመንት ከአራት ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚልቅም ይገመታል።
በአፍሪካ የሞባይል የገንዘብ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ480 ሚሊዮን በላይ ተሻግሯል።
ዲጂታል ስርዓቱን የሚያሳልጡ መሰረተ ልማቶች እና የዳታ ማዕከላት በአፍሪካ መንግስታት እና የልማት አጋሮች ትብብር እየተገነቡ ነው።
ዲጂታል ኢኮኖሚ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለትምህርት እና ክህሎት፣ ለመንግስት የአሰራር ውጤታማት፣ ለፋይናንስ አካታችነት እና ኮሙኒኬሽን ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከእ.አ.አ 2020 በፊት የዲጂታል ምህዳሯ የተገደበ ነው ማለት ይቻላል። ዝቅተኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ተደራሽነት፣ ለቴሌኮም አገልግሎት ከፍተኛ ክፍያ ወጪ የሚወጣበት እና በቴሌኮም አገልግሎት የመንግስት ብቻ የበላይነት የሚታይበት ነበር።
ከለውጡ በኋላ መንግስት የቅድሚያ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አማካኝነት ዲጂታል ተጠቃሽ ነው።
የዲጂታል ዘርፍ ከብዝሃ የኢኮኖሚ ምንጮች አንዱ ሆኖ ነው።ዲጂታላይዜሽን ለኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ አካታች የሆነ የዲጂታላይዜሽን ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ካስገባች ሰነባብታለች።
ኢትዮጵያ ከእ.አ.አ 2020 አንስቶ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በማዘጋጀት ስተገብር ቆይታለች።
ስትራቴጂው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እና መንግስታዊ አገልግሎቶችን ዲጂታል የማድረግ አላማ ያደረገ ነው።
በዚህም 900 ገደማ የሚሆኑ መንግስታዊ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ ሆነዋል።3000 የሚሆኑ የዲጂታል አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አግኝተዋል። የፋይዳ መታወቂያ ኢኒሼቲቭ አማካኝነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ሆነዋል።
የሞባይል እና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። የአራተኛ እና አምስተኛው ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት እየሰፋ መጥቷል።የዲጂታል ክህሎትም ተስፋ ሰጪ እድገት ታይቶበታል።
የቴሌኮም ዘርፉ ለውጭ ክፍት እንዲሆን መንግስት ባስቀመጠው የፖሊሲ አቅጣጫ መሰረት ሳፋሪኮም ኩባንያ የቴሌኮም አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን “ምፔሳ” የተሰኘ የሞባይል የገንዘብ አገልግሎት እየሰጠም ይገኛል።
የመንግስት የዲጂታል ፖሊሲዎች እና የህግ ማዕቀፎች ለዘርፉ ምቹ ምህዳር በመፍጠር ትስስር እንዲሰፋ እና አገልግሎቶች እንዲዘምኑ አስችሏል።
ኢትዮጵያ ከአምስት በፊት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በማቋቋም በርካታ ስራዎችን አከናውናለች።
ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በክረምት መርሃ ግብር (ሰመር ካፕም) ወጣቶች ሲማሩ እንደቆዩ አውስተው በዘርፉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።
ሁሉንም ዘርፍ የሚነካው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በግብርና፣ጤና፣ አገልግሎት እና ሌሎች ዘርፎች ላይ በመግባት ስራን እያቀላጠፈ ይገኛል።
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት የሚሰበሰቡ ዳታዎች ለመንግስት እና ግል ተቋማት አገልግሎት ላይ እየዋሉ እንደሚገኝም ተገልጿል።
መንግስት ወጣቶች በሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት ሀገርን አልፎም ዓለምን የሚጠቅሙ ችግር ፈቺ ስራዎችን እንዲያቀርቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ቴሌብር፣ መሶብ እና ዘመንን ጨምሮ ያሉ የዲጂታል አገልግሎቶች የዘርፉን እድገት በማሳለጥ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት የዲጂታል 2030ን ስትራቴጂ ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የታለመለትን ግብ አሳክቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል።ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 በይፋ ያበሰሩ ሲሆን ተደራሽነትን ማስፋት፣ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን ማጎልበት ደግሞ የስትራቴጂው ቁልፍ መሰረታዊ ትልሞች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽ፣ ፍትሃዊ እና አስተማማኝ የዲጂታል ምህዳር መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ም ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን መሰረት በማድረግ መዘጋጀቱን አንስተዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ሦስት ቁልፍ ትልሞች እንዳሉት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህም ተደራሽነትን ማስፋት፤ እኩል እድል ማመቻቸትና በተቋማትና ህዝብ መካከል መተማመንን መፍጠር መሆናቸውን አብራርተዋል።
ትልሞቹ እንዲሳኩም በተለይ የህዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማት ማስፋት ላይ ትልቅ ስራ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ይህም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ሰው ተኮር ሆኖ የዜጎችን ኑሮ እንዲያሻሽል ትልቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በአጠቃላይ በዲጂታል ኢትዮጵያ የሚከናወኑ ስራዎች የመደመር መንግስት በቀለለ ቢሮክራሲ ታላላቅ ስትራቴጂዎችን እውን ለማድረግ ከያዘው ግብ ጋር የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 እንዲሳካም ሁሉም በትብብር መስራት እንዳለበት ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት፥ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 በቴሌኮም ዘርፍ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው።
ለአብነትም የሞባይል ደንበኞች ቁጥርን 97 ሚሊዮን ማድረስ የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 57 ሚሊዮኑ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ሆነዋል ሲሉ አንስተዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አክለው እንደገለጹት፥ አንድ ሺህ ሰላሳ ከተሞችም የ4ጂ ኔትወርክ ተደራሽ ሆነዋል ነው ያሉት።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሞባይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር 128 ሚሊዮን የሚደርስ ሲሆን፣ የ5ጂ ኔትወርክ ሽፋንን 100 ከተሞች ይደርሳል ብለዋል።
በ2030 የዲጂታል ክፍያን ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር አሁን ካለበት ከሰባት እጥፍ በላይ እንዲያድግም በልዩ ትኩረት ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል።ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት፣ አካታችነት እና ማህበራዊ ለውጥ ቁልፍ ምሰሶ ነው።
ስትራቴጂው በሚገባ ከተተገበረ፣ በቂ የዲጂታል መሰረተ ልማቶች ከተገነቡ እና ዜጎች በንቃት ከተሳተፉ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን ትሩፋቶች ተጠቅማ ትልሞቿን ማሳካት እንደምትችል አያጠራጥርም።