የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ ሊያከናውኑ ይገባል - የትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ ሊያከናውኑ ይገባል - የትምህርት ሚኒስቴር
አሶሳ፤ ታህሳስ 13/2018(ኢዜአ)፦ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ ሊያከናውኑ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር አስገነዘበ።
3ኛው የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዛሬ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት በትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ሥራቸው በተጓዳኝ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን በተለያዩ ዘርፎች ማህበረሰብ ተኮር ለውጥ እንዲያመጡ እየተደረገ ነው።
በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች የልህቀት ማዕከል ሆነው በሚያከናውኑት የጥናትና ምርምር ስራ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በተለይም የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች በተቀናጀ አግባብ በየአካባቢው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ተልዕኳቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት ሰብሳቢና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኡባህ አደም(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ፎረሙ ዩኒቨርሲቲዎቹ በጋራ በሚያከናውኗቸው የምርምር ስራዎች ላይ ተሞክሮ ለመቀመርና የተከናወኑ የምርምር ስራዎችን ውጤታማነት ለመገምገም የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ ተኮር የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተግባር ተኮር መስክ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በግብርና፣ በማዕድንና የተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ከማል አብዱራሂም(ዶ/ር) ናቸው።
በተለይም በማንጎ እና ቀርከሃ ሀብት ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ የምርምር ስራዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ያሳደጉ ስራዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
በፎረሙ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች፣ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች የትምህርቱ ዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።
የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም 15 ዩኒቨርሲቲዎችን ያቀፈ ሲሆን አንደኛ ፎረሙን በድሬዳዋ እእንዲሁም ሁለተኛውን በአርሲ ዩኒቨርሲቲዎች ማካሄዱ ይታወሳል።