የበጋ ወራት መስኖ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የበጋ ወራት መስኖ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጠ ነው
ገንዳ ውኃ፣ ታህሳስ 13/2018 (ኢዜአ):-በምዕራብ ጎንደር ዞን የበጋ ወራት መስኖ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ መሆኑን የልማቱ ተሳታፊ የገንዳ ውኃ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በዞኑ በዘንድሮ የበጋ ወራት የመስኖ ልማት እንቅስቃሴ 2 ሺህ 400 ሄክታር ማልማት ተችሏል።
የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እነየ ዓለሙ እንዳሉት፤ በከተማው ዙሪያ እየለማ የሚገኘው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በገበያው ይስተዋል የነበረውን የአቅርቦት ክፍተት እየሞላ ነው።
ከዚህ በፊት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶቹ ከጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች ይመጡ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ ከዚሁ በሚመረተው ምርት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።
በዚህም ሰላጣ፣ የሃበሻ ጎመንና ቲማቲም በበቂ አቅርቦትና ተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
በበጋው ወራት የመስኖ ልማት ፓፓያ፣ ሃባብና ዘይቱን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንድያገኙ እንዳስቻላቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ምህረቱ ናቸው።
"የመስኖ ልማት እየተለመደ መምጣት በገበያው ላይ በአቅርቦትና በዋጋ ለሸማቹ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ነው ያሉት።
በበጋ መስኖ ልማት 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት በተለያዩ አትክልት እያለማ መሆኑን የገለፀው ወጣት ተገኘ ወርቁ
በቀጣይ ምርቱን ወደ ገበያ ለማቅረብ ቲማቲም፣ ቃሪያ እና ሽንኩርትን ማልማቱንም ገልጿል።
በልማቱ ከ400 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚጠብቅ ጠቅሶ፤ ይህም የመስኖ ልማት ከመኸር ሰብል ልማት ጎን ለጎን ትርፋማ የሚያደርግ መሆኑን አስረድቷል።
የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ግብርናና አካባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማንደፍሮ ተፈራ እንዳሉት፤ በከተማ ግብርና የመስኖ ልማት 410 ሄክታር መሬት በከተማው ማልማት ተችሏል።
የከተማ ግብርና መስፋፋትም ማህበረሰቡ የተለያዩ አይነት አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በቀላሉ ለማግኘት ከማስቻሉም በላይ የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየበረከተ እንደሆነ ገልፀዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ጤናው ፋንታሁን እንዳሉት፤ በበጋ መስኖ ልማት በአንደኛ ዙር 4 ሺህ 925 ለማልማት ታቅዶ እስካሁን ከ2 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል።
ከዚህ ውስጥ ከ800 ሄክታር በላዩ በቋሚ አትክልት እና ፍራፍሬ የለማ ሲሆን ከለማው መሬትም ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ምርቱ ለአካባቢው ገበያና አጎራባች ዞኖች እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፤ አልሚውንም ሆነ ሸማቹን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን አንስተዋል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ከ2 ሺህ 900 በላይ መሬት ለምቶ ከ450 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።